👉”…ዛሬ አሸንፈናል ማለት ሁሉም ነገር ልክ ነው ማለት ግን አይደለም” ውበቱ አባተ
👉”በጨዋታው በታየው እንቅስቃሴ ኢትዮጵያ ባታሸንፍ ኖሮ ውጤቱ ፍትሀዊ አይሆንም ነበር” – ሰርዲዮቪች ሚሉቲን ሚቾ
በዋልያዎቹ አሸናፊነት ከተጠናቀቀው የአቋም መፈተሻ ጨዋታ በኋላ የብሔራዊ ቡድኖቹ ዋና አሠልጣኞች ተከታዩን የድህረ-ጨዋታ አስተያየት ሰጥተውናል።
ውበቱ አባተ – ኢትዮጵያ
ቡድኑ ስላደረጋቸው ሁለቱ የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎች እና ድል ስላገኙበት የዛሬው ጨዋታ?
ሁለቱ የወዳጅነት ጨዋታዎች የተዘጋጁት በቀጣይ ላለብን የማጣርያ ጨዋታ በተሻለ አቅማችንን ለመገምገም ነበር። ከዚህ አንፃር ጨዋታዎቹን በጥሩ ሁኔታ ተጠቅመንባቸዋል። የያዝናቸውን ተጫዋቾች በሙሉ ኢኮኖሚካል ሆነን ለመጠቀም ሞክረናል። እንደአጠቃላይ በብዙ ያተረፍንባቸው ጨዋታዎች ናቸው። ከባለፈው የሴራሊዮን ጨዋታ ዛሬ በተሻለ የጨዋታ ብልጫ ኖሮን ዕድሎችን መፍጠር ችለናል። አሁንም ቢሆን አጨራረስ ላይ መጠነኛ መሻሻል የሚገባቸው ነገሮች ቢኖሩም ተጋጣሚያችን ዩጋንዳ ጠንካራ ቡድን እንደመሆኑ ዕድሎች ፈጥረን ሁለት ግቦችን ማስቆጠራችን እንደ ጠንካራ ሂደት እንመለከተዋለን።
ዕድሎችን በመፍጠሩ ረገድ ከሲራሊዮኑ ጨዋታ በተሻለ በዛሬው ጨዋታ ስለመሻላቸወ…?
የቤት ግንባታ ከጣርያ አይጀምርም። በተመሳሳይ ስንጀምር በመከላከል አደረጃጀታችን ላይ ብዙ ክፍተቶች ነበሩብን። በመሆኑም እነሱ ላይ በርካታ ስራዎችን ስንሰራ ነበር። በዚህም ረገድ መሻሻሎችን ማሳየት ጀምረናል። ቀጥሎ ደግሞ ዕድሎች መፍጠር ላይ በትኩረት እየሰራን ነው። በሴራሊዮኑ ጨዋታ ብዙም ባይሆኑ መሻሻሎች ነበሩ። የተፈጠሩ የግብ እድሎችን ወደ ግብ ለመቀየር ደግሞ ጎል እንደዚህ አስቆጥሩ ብለህ አታስተምርም። ነገርግን አዕምሯቸው ላይ አጋጣሚ ሲገኝ እንዲረጋጉ እና በእራሳቸው እንዲያምኑ ለማድረግ ስራዎችን እየሰራን እንገኛለን። ዛሬ አሸንፈናል ማለት ሁሉም ነገር ልክ ነው ማለት ግን አይደለም። የሚቀሩትን እናርማለን። በሁለቱም ጨዋታዎች የተመለከትኩት በቡድኑ ላይ መሻሻል እንዳለ ነው።
በሁለቱ ጨዋታዎች ውጤት ደስተኛ ስለመሆኑ እና ቡድኑ ለጋና ጨዋታ ዝግጁ ስለመሆኑ..?
እኔ በመጀመሪያ ደስተኛ የሚያደርገኝ ነገር ተጫዋቾቹ ለመቀበል እና ለሥራ ያላቸው ፍላጎት እና ተነሳሽነት ነው። ለሀገራቸው አንድ ነገር ሰርተው ለማለፍ ያላቸው ፍላጎት አስደሳች ነው። ለመጫወት የምንፈልገበት መንገድ እንደተመለከታችሁት ማንንም ደስተኛ ያደርጋል። ይህ ማለት ግን ሁሉ ነገር የበቃ ነው ማለት አይደለም። ሌሎች የሚጎሉን ብዙ ነገሮች አሉ። ለምሳሌ ዛሬ የገጠምነው ዩጋንዳ በፊፋ ደረጃ ከእኛ በጣም የተሻለ ነው። እኛ ወደእነሱ ደረጃ መጠጋት መቻል አለብን። ይህ ቁጭት ወደ ልጆቹ እንዲገባ እየሰራን ነው። በእስካሁኑ ሂደታችን ግን በጣም ደስተኞች ነን።
ሰርዲዮቪች ሚሉቲን ሚቾ – ዩጋንዳ
ስለጨዋታው…?
ከኢትዮጵያ ጋር አስፈላጊ የሆነና የተጫዋቾቻችንን የአፈፃፀም ደረጃ ያየንበት ጨዋታ አድርገናል። ከጥቂት የልምምድ ጊዜያት በኋላ ነው የመጣነው። እኔ እንደማምነው የወዳጅነት ጨዋታው እንደ ልምምድ ነፃ ነው። ተጫዋቾች በነጥብ ጨዋታዎች ላይ እንደሚደበቁበት ዓይነት አይደለም። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ይህንን ዕድል ስለሰጠን ደግሞ እናመሰግናለን። ሁኔታዎችን መዝነን አዳዲስ ነገሮችን በመሞከር እና በማየት ለሚጠብቀን የኬኒያው ጨዋታ የሚያስፈልገንን እናዘጋጃለን። በእግርኳስ ታሸንፋለህ ወይም ትምህርት ትወስዳለህ። እኛም ጨዋታውን መሸነፋችን ደስ የሚያሰኝ ባይሆንም የተማርናቸው ነገሮች አሉ። ለቀጣዩ ጨዋታ ብቁ የሆኑ ተጫዋቾችን አይተናል። የደከሙትንም አይተናል። በውጪ ሀገራት የሚጫወቱ ተጫዋቾች ሲቀላቀሉን ደግሞ የተሻለ ተፎካካሪ ቡድን እንደሚኖረን እናምናለን። በዚህ ጨዋታ ላይ የሞከርናቸውን ነገሮች በማጎልበትም በኬኒያው ጨዋታ ውጤት ይዘን ለመውጣት እንጥራለን። ኢትዮጵያዊያን ስላሸነፉ እንኳን ደስ ያላችሁ ማለት እፈልጋለው። በዛው መጠንም ለተደረገልን አቀባበል እና እንክብካቤ ማመስገን እፈልጋለሁ። በዚህ አጋጣሚ ለአፍሪካ ሀገራት ዋንጫ በማለፋቸውም እንኳን ደስ ያላችሁ ማለት እፈልጋለሁ።
የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ስለተወሰደባቸው…?
ይህ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን መገለጫው ነው። እኛ ደግሞ ተዳክመን የታየነው በዚሁ ነጥብ ላይ ነው። ሜዳው ሰፊ እንዲሆንላቸው ፈቅደናል። ከአንዱ መስመር ወደ ሌላው ኳስ እንዲያሻግሩ እና ወደ ውስጥም ሰብረው እንዲገቡ ፈቅደን ነበር። ይህንን በቀጣይ በጣም ማስተካከል ይኖርብናል። ለተጫዋቾቼም አንድ ተጫዋች ብቻ ጫና እንዲፈጥር አድርጎ ከመከላከል ይልቅ እንደቡድን ጫና መፍጠሩ ኳስ ለመንጠቅ እና ለማሸነፍ የሚረዳው ብቸኛው መንገድ እንደሆነ ነግሬያቸው ነበር። በድጋሚ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እንኳን ደስ ያላችሁ ማለት እወዳለሁ። እኛም የታዩብንን ድክመቶች አስተካክለን መቅረብ ይጠበቅብናል።
ስለውጤቱ ፍትሀዊነት…?
አዎ በትክክል ፤ ማሸነፍ ይገባቸው ነበር ። በእርግጥ እግርኳስ ነው እና እኛም ግብ አስቆጥረናል። ነገር ግን በጨዋታው በታየው እንቅስቃሴ ኢትዮጵያ ባታሸንፍ ኖሮ ውጤቱ ፍትሀዊ አይሆንም ነበር። የስፖርት ሰው መሆን እና እውነታውን መቀበል ይኖርብኛል። እኛም ከጨዋታው ትምህርት ወስደን የምንቀጥል ይሆናል።