ዋልያዎቹ ከጋና ጋር ጨዋታቸውን የሚያደርጉበት ከተማ ገብተዋል

በአሠልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የምድብ የመጀመሪያ ጨዋታውን ለማድረግ ከደቂቃዎች በፊት ኤልሚና ከተማ ደርሷል።

ለኳታሩ የዓለም ዋንጫ ለማለፍ የምድቡ ሁለት የማጣሪያ ጨዋታዎችን በቀናት ልዩነት የሚያደርገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከነሐሴ 4 ጀምሮ ዝግጅቱን አዳማ ላይ ሲሰራ እንደነበር ይታወሳል። ለቀናት በአዳማ ኤክስኪዩቲቭ ሆቴል ማረፊያውን በማድረግ ሲዘጋጀ የነበረው ስብስቡም በቅድሚያ ከጠራቸው 23 ተጫዋቾች ሙጂብ ቃሲም እና ሀይደር ሸረፋን በግል ጉዳዮች ምክንያት እንዲሁም ሀብታሙ ተከስተን በጉዳት ምክንያት ከስብስቡ ውጪ አድርጎ እንደነበር ይታወቃል። አሠልጣኝ ውበቱ አባተ እና ረዳቶቻቸው በአስገዳጅ ሁኔታ የወጡትን ተጫዋቾች ለመተካትም ቸርነት ጉግሳን እና በዛብህ መለዩን በመጥራት ልምምድ ሲያሰሩ ቆይተዋል።

ለወሳኞቹ የምድብ የመጀመሪያ ጨዋታዎች ይረዳው ዘንድ ሀሙስ ከሴራሊዮን ከትናንት በስትያ ደግሞ ከዩጋንዳ ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ያደረገው ቡድኑም ትናንት ከሰዓት (8 ሰዓት) ከባህር ዳር ወደ አዲስ አበባ ጉዞ እንዳደረገ ተገልፆ ነበር። ትናንት እንደተገለፀው በዛብህ መለዮ፣ ሱራፌል ዳኛቸው፣ ፍፁም ዓለሙ፣ ዊልያም ሠለሞን እና ፍሬው ጌታሁን ከስብስቡ ውጪ ሆነዋል። ከአምስቱ ተጫዋቾች ውጪ ያሉት 23ቱ ተጫዋቾች ግን የጋና እና ዚምባቡዌ ጨዋታ የሚያደርገው የመጨረሻ ዝርዝር ውስጥ በመግባታቸው በትናንትናው ዕለት የህክምና ምርመራ በማድረግ አዳራቸውም በጁፒተር ኢንተርናሽናል ሆቴል ካደረጉ በኋላ ዛሬ ረፋድ ወደ ጋና ተጉዘዋል።

21 ተጫዋቾች፣ 10 የአሠልጣኝ ቡድን አባላት፣ አንድ የቡድን መሪ እና አንድ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ በአጠቃላይ 35 የልዑካን ቡድን በመያዝ ወደ ጋና የተጓዘው ስብስቡም 7:50 ሲል አክራ አየር ማረፊያ ደርሷል። ስብስቡ በስፍራው እንደደረሰም የኮቪድ-19 ምርመራ እንደተደረገለት ለማወቅ ተችሏል። ከምርመራው በኋላ ደግሞ ጨዋታው ወደሚደረግበት እና ከአክራ 148 ኪሎ ሜትሮችን ርቃ ወደምትገኘው ኤልሚና ከተማ የመኪና ጉዞ እንዳደረገ ሶከር ኢትዮጵያ ከስፍራው ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።

ቡድኑም 2:40 ከቆየው የመኪና ጉዞ በኋላ ከደቂቃዎች በፊት (3:30) ኤልሚና ከተማ ደርሷል። ብሔራዊ ቡድኑም ማረፊያውን በኤልሚና ቢች ሪዞርት እንዳደረገ አረጋግጠናል። አሠልጣኝ ውበቱ አባተም በነገው ዕለት ቡድኑን ልምምድ እንደሚያሰሩ ተጠቁሟል።