የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አማካይ ሽመልስ በቀለ ከግብፁ ክለብ ምስር ለል መቃሳ ጋር ስለመለያየቱ መረጃዎች እየወጡ ይገኛሉ።
ከሰባት ዓመታት በፊት የሱዳኑን ኤል ሜሪክ በመልቀቅ ለግብፁ ፔትሮጀት ፊርማውን አኑሮ የእግርኳስ ህይወቱን በግብፅ ሊግ የቀጠለው የአማካይ አጥቂው ሽመልስ ለስድስት ዓመታት በክለቡ ከተጫወተ በኋላ 2019 ላይ ወደ ሌላኛው የሀገሪቱ ክለብ ምስር ለል መቃሳ አምርቶ እንደነበር ይታወቃል። ተጫዋቹም በወቅቱ እስከ 2023 ድረስ የሚያቆየውን ውል ፈርሞ ግልጋሎት ሲሰጥ ነበር።
መቃሳን ከተቀላቀለ በኋላ 61 ጨዋታዎች በግብፅ ከፍተኛው የሊግ እርከን ያደረገው ተጫዋቹ 16 ጎሎችን እና 6 ለግብ የሆኑ ኳሶችን በስሙ እንዳስመዘገበ መረጃዎች ይጠቁማሉ። አሁን ላይ የግብፅ ብዙሃን መገናኛዎች እያወጡት እንዳለው መረጃ ከሆነ የአንድ ዓመት ቀሪ ኮንትራት የሚቀረው ሽመልስ ከክለቡ ጋር በስምምነት መለያየቱን ይጠቁማሉ።
ይህ ጉዳይ እውነት ነው ወይ ብለን ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድኑ ጋር ወደ ጋና ያመራውን ሽመልስን ስንጠይቀውም “ጉዳዩ ገና ነው። ሰሞኑን ግን የሚፈጠሩ አዳዲስ ነገሮች አሉ።” በማለት አጭር ምላሽ ሰጥቶናል።