ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የተመለሰው መከላከያ የአጥቂ አማካይ እና የመስመር ተጫዋቹን በአንድ ዓመት ውል የግሉ አድርጓል።
የነባር ተጫዋቾችን ውል በማደስ የክረምቱን የዝውውር መስኮት የጀመሩት መከላከያዎች በርካታ አዳዲስ ተጫዋቾችን እያስፈረሙ እንደሆነ ይታወቃል። ክለቡም በዋና አሠልጣኙ ዮሐንስ ሳህሌ እየተመራ ቢሾፍቱ ላይ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን ከጀመረ ቀናቶች ተቆጥረዋል። ሶከር ኢትዮጵያ አሁን ባገኘችው መረጃ ክለቡ የመስመር ተጫዋቹ ቢኒያም በላይን ማስፈረሙን ያመላክታል።
ቢኒያም በ2009 መጨረሻ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ለቆ ወደ ጀርመን አምርቶ የሙከራ ጊዜ ማሳለፉ የሚታወስ ሲሆን ወደ አልባንያው ክለብ ስከንደርቡ አምርቶም ከክለቡ ጋር የሊግ ዋንጫን ማንሳቱ አይዘነጋም። በመቀጠል ወደ ስዊድን በማቅናት ለስሪያንስካ እና ኡሚያ ክለቦች የተጫወተ ሲሆን በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን አጋማሽ ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ ለሲዳማ ቡና ተጫውቶ ነበር። አሁን ደግሞ በአንድ ዓመት ውል በጦሩ መለያ የእግርኳስ ህይወቱን ለመቀጠል በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ተገኝቶ ፊርማውን አኑሯል።