ንግድ ባንክ ከፍፁም የጨዋታ ብልጫ ጋር የዛንዚባሩን ክለብ አሸንፏል

ኬንያ ላይ የሴካፋ ዞን የቻምፒየንስ ሊግ የማጣሪያ ውድድር እያደረገ የሚገኘው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዛንዚባሩን ክለብ ኒው ጄኔሬሽንስን 10-1 በሆነ ውጤት አሸንፏል።

አሠልጣኝ ብርሃኑ ግዛው እሁድ ድል ከተቀዳጁበት ጨዋታ ሁለት ለውጦችን አድርገው የዛሬውን ጨዋታ ቀርበዋለወ። በዚህም ታሪኳ ዴቢሶ እና እመቤት አዲሱን አሳርፈው አለምነሽ ገረመው እና የምስራች ላቀውን ወደ ቀዳሚ አሰላለፍ አምጥተዋል።

የጨዋታውን የሀይል ሚዛን ወደ ራሳቸው አድርገው መጫወት የጀመሩት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በ8ኛው ደቂቃ መሪ የሆኑበትን ኳስ ከመረብ አገናኝተዋል። በዚህም የቡድኑ አምበል ሎዛ አበራ ወደ መሐል ሜዳ በመሳብ ያገኘችውን ኳስ በተከላካዮች መሐል ለመዲና ዐወል አመቻችታላት ፈጣኗ የመስመር አጥቂ ኳሱን በጥሩ ሁኔታ ከመረብ ጋር አዋህዳዋለች። ገና በጊዜ መሪ የሆኑት ባንኮች ከደቂቃ በኋላም የግቡን ኳስ አመቻችታ ባቀበለችው ሎዛ አማካኝነት ሌላ ጥቃት ቢፈፅምም የኒው ጄኔሬሽኗ የግብ ዘብ ዙና ያሲን እና የግቡ አግዳሚ ተባብረው ኳሱን አምክነውታል።

አሁንም ጫና ማሳደራቸውን የቀጠሉት የአሠልጣኝ ብርሃኑ ተጫዋቾች በ15ኛው ደቂቃ በሎዛ እንዲሁም በ16ኛው ደቂቃ በሰናይት አማካኝነት የሰሉ ጥቃቶችን ፈፅሞ ነበር። የባንክን ጥቃት መቋቋም የተሳናቸው ኒው ጄኔሬሽንሶች በበኩላቸው ከኳስ ጀርባ በመሆን መጫወትን ቢመርጡም በ19ኛው ደቂቃ አቻ የሆኑበትን ጎል አግኝተዋል። በተጠቀሰው ደቂቃም የመሐል ተከላካዩዋ ሀሳቤ ሙሶ በአግባቡ ያላፀዳችውን ኳስ ሀስና ምፓንጃ አግኝታው በአስደናቂ ሁኔታ ታሪኳ በርገና መረብ ላይ አሳርፋዋለች።

ጨዋታው 25ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስም አረጋሽ ካልሳ የግል ጥረቷን ተጠቅማ ከመሐል ሜዳ እየገፋች የሄደችውን ኳስ ከሳጥን ውጪ መትታው ቡድኗን ዳግም መሪ ልታደርግ ነበር። ከስምንት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ሎዛ አበራ የተላከላትን ረጅም ኳስ አግኝታ ጎል አስቆጥራለች። መሪነቱን ያገኙት ባንኮች ከደቂቃ በኋላም መሪነታቸውን ወደ ሦስት ከፍ አድርገዋል። በዚህም የኒው ጄኔሬሽን ተከላካዮች ኳስ ከግብ ክልላቸው ሲመሰርቱ የመጀመሪያውን ጎል ያስቆጠረችው መዲና ደርሳ ኳስ በመንጠቅ ለሎዛ ካቀበለቻት በኋላ ቀድመው የተቆጠሩት ግቦች ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ ያደረገችው አጥቂ ለራሷ ሁለተኛ ለቡድኗ ሦስተኛ ግብ አስቆጥራለች።

የመጀመሪያ አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ሲቀረው ወደ ቀኝ ባዘነበለ መስመር የቅጣት ምት ያገኙት ንግድ ባንኮች አጋጣሚውን በአረጋሽ ካልሳ አማካኝነት ወደ ግብ ሲልኩት የግብ ዘቧ ዙና ያሲን በሚገባ መቆጣጠር ተስኗት ኳሱ መረብ ላይ አርፎ ባንክ አራት ለአንድ እየመራ ወደ እረፍት አምርቷል።

የሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረም ጫና ማሳደራቸውን የቀጠሉት ባንኮች በ48ኛው ደቂቃ የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተው መሪነታቸውን አሳድገዋል። በዚህም ሎዛ አበራ ራሷ ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ወደ ግብነት ቀይራዋለች። ጨዋታው ከቁጥጥራቸው ውጪ እየሆነ የመጣው ኔው ጄኔሬሽንሶች ወደ ጨዋታው ለመመለስ የግብ ክልላቸውን ነቅለው ቢወጡም ከጥቅም ይልቅ ጉዳት አጋጥሟቸዋል። በ58ኛው ደቂቃም ቡድኑ እጅግ ወደ መሐል ተጠግቶ በሚጫወትበት ጊዜ ህይወት ደንጊሶ ከተከላካዮች ጀርባ የጣለችውን ኳስ ሎዛ አበራ በማግኘት ጎል አድርጋዋለች።

በሁለተኛው አጋማሽ አንድም ጊዜ ወደ ባንክ የግብ ክልል ያልደረሰው የዛንዚባሩ ክለብ በ73ኛው ደቂቃ ማስተዛዘኛ ግብ ባስቆጠረችው አጥቂ ሁስና ምፓንጃ አማካኝነት ጥቃት ፈፅመዋል። ነገርግን ተጫዋቿ የመታችው ኳስ ለታሪኳ እምብዛም ሳያስቸገርግ ቀርቷል። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ከመዓዘን የተሻገረው ኳስ ከተከላካዮች ተጨርፎ ሲመለስ ያገኘችው ሎዛ ወደ መሐል የመታችውን የመሬት ለመሬት ኳስ ሀሳቤ ሙሳ አግኝታ ወደ ግብነት ቀይራ ንግድ ባንክ ሰባተኛ ጎል አግኝቷል።

ሙሉ የጨዋታው ክፍለ ጊዜው ሊጠናቀቅ ስድስት ደቂቃዎች ሲቀሩት ደግሞ ጨዋታው ሦስት ግቦችን አከታትሎ አስተናግዷል። በቅድሚያም የጨዋታውን የመጀመሪያውን ጎል ያስቆጠረችው መዲና በ84 እና በ86 ደቂቃ ሁለት ጎሎችን አከታትላ አስቆጥራለች። በመቀጠል ደግሞ ሎዛ አረጋሽ ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን ሁለተኛ የፍፁም ቅጣት ምት ለራሷ ስድስተኛ ለቡድኗ ደግሞ አስረኛ ጎል አድርጋዋለች። ጨዋታውንም ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 10-1 በሆነ ውጤት አሸናፊ አድርጓል።ያጋሩ