ወልቂጤ ከተማ ለ2014 የሊጉ ውድድር ዝግጅት የሚያደርጉበት ቦታ እና የሚጀምሩበት ቀን ታውቋል።
ከሊጉ ወርዶ የነበረ ቢሆንም በድጋሚ ያገኘውን ዕድል በመጠቀም የቤትኪንግ የኢትዮጽያ ፕሪምየር ሊግ መቆየት የቻለው ወልቂጤ ከተማ የአሠልጣኙ ጳውሎስ ጌታቸውን ውል ካደሰ በኋላ ጥቂት ተጫዋቾች በማዘዋወር ቆይቶል። ቀደም ብሎ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን ለመጀመር አስቦ የነበረው ክለቡ በተለያዩ ምክንያቶች ቀኑን ገፍቶ የፊታችን እሁድ ነሐሴ 30 ተጫዋቾቹን እንደሚሰበስብ ለማወቅ ተችሏል። የክለቡ ተጫዋቾች ሰኞ ወደ ሀዋሳ የሚያመሩ ሲሆን አጠቃላይ የህክምና ምርመራ ተደርጎላቸው መደበኛ ልምምዳቸውን እንደሚጀምሩም ተጠቁሟል።
በተያያዘ ዜና የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ባሳለፍነው ሳምንት ከክለቡ አመራሮች ጋር ባደረገው ውይይት ቡድኑን በዓይነት እንዲሁም በገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ስምምነት የደረሱ ሲሆን ይህም ቡድኑ የሚያጋጥሙትን ችግሮች በቅርብ ሆኖ ለመፍታት እንዲረዳው ታስቦ የተደረገ ስምምነት መሆኑ ተገልጿል።