የቀድሞ የፈረሰኞቹ የአጥቂ አማካይ የጣና ሞገዶቹን ለመቀላቀል ተስማምቷል

በኬንያ ሊግ የውድድር ዓመቱን ያሳለፈው የቀድሞ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋች ባህር ዳር ከተማን ለመቀላቀል ስምምነት ላይ ደርሷል።

በአሠልጣኝ አብርሃም መብራቱ የሚመሩት ባህር ዳር ከተማዎች በ2014 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተጠናክሮ ለመቅረብ በንቃት በዝውውር ገበያው ላይ በመሳተፍ በያዝነው ሳምንት የመጀመሪያ ቀናት የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን እንደጀመሩ ይታወቃል። ሶከር ኢትዮጵያ አሁን ያገኘችው መረጃ ደግሞ ከዚህ ቀደም በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያን እግርኳስ የተዋወቀውን አብዱልከሪም ንኪማን ክለቡ ለማስፈረም የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ መሆኑን ይጠቁማል።

ቡርኪናፋሶዋዊው የአጥቂ አማካይ ንኪማ 2009 ላይ የመዲናውን ክለብ ከተቀላቀለ በኋላ በበርካታ የክለቡ ደጋፊዎች ተወዳጅ መሆን መቻሉ የሚታወስ ሲሆን በመጣበት ዓመትም የሊጉን ዋንጫ አሸንፎ እስከ 2010 ድረስ ግልጋሎት ሰጥቶ ጋንድዛሳር ካፓን ለተባለ የአርሜንያ ክለብ ፊርማውን አኑሮ መጫወት ቀጥሎ ነበር። ተጫዋቹ ዘንድሮ የኬንያው ክለብ ጎር ማህያን ለማገልገል የሁለት ዓመት ውል ፈርሞ ከቀናቶች በፊት የተጠናቀቀውን የውድድር ዓመት ያሳለፈ ቢሆንም ከክለቡ ጋር በስምምነት በመለያየት ዳግም ወደ ኢትዮጵያ የሚመልሰውን ዝውውር ለመፈፀም መስማማቱ ታውቋል።

በአሁኑ ሰዓት ለእረፍት ሀገሩ የሚገኘው ተጫዋቹ መስከረም 3 ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በይፋ ፊርማውን ለጣና ሞገዶቹ ካኖረ በኋላ አዲሶቹ አጋሮቹን በመቀላቀል የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን እንደሚጀምር ድረ-ገፃችን አረጋግጣለች።