በተጠናቀቀው ግማሽ ዓመት ጅማ አባጅፋርን ተቀላቅሎ የነበረው ግዙፍ አጥቂ ወደ ህንድ ሊግ ማምራቱ ታውቋል።
ጋናዊው የአጥቂ መስመር ተጫዋች ራሂም ኦስማኖ በተጠናቀቀው የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ አጋማሽ ላይ በአሠልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም የሚመራው ጅማ አባጅፋርን ተቀላቅሎ ግልጋሎት መስጠቱ ይታወሳል። ዓምና ለስሑል ሽረ ፈርሞ የነበረ ኦስማኖ በአካባቢው በተፈጠረው ችግር ክለቡ በፕሪምየር ሊጉ ባለመሳተፉ ሳይጫወት መቅረቱም ይታወቃል።
ከኢትዮጵያ ውጪ በዛምቢያ እና አልጄሪያ ተጫውቶ ያሳለፈው አጥቂውም በዛሬው ዕለት የህንዱን ክለብ ጎኩላም ኬራላን በአንድ ዓመት ውል ተቀላቅሏል። ዝውውሩን ተከትሎም ኦስማኖ በህንድ ሊግ የሚጫወት ሁለተኛው (ከአዋል መሐመድ በመቀጠል) ጋናዊ ሆኗል።