ኢትዮጵያዊያን ዳኞች የአህጉሪቱን ጨዋታዎች ይመራሉ

በርከት ያሉ የሀገራችን ዳኞች የአህጉሪቱን የቻምፒየንስ ሊግ እና ኮንፌዴሬሽን ውድድሮች እንደሚመሩ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።

የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን እና ቻምፒየንስ ሊግ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎቸ ከቀናት በኋላ እንደሚጀመሩ መገለፁ ይታወቃል። በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የሚደረጉትን ጨዋታዎች የሚመሩ ዳኞች ሲታወቁም በርከት ያሉ ኢትዮጵያዊያን አልቢትሮች ጨዋታዎችን እንዲያጫውቱ መመደባቸው ተገልጿል።

ከደቂቃዎች በፊት (10 ሰዓት) በሊቢያ እና ጋቦን መካከል መደረግ የጀመረውን የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ባምላክ ተሰማ ከረዳቶቹ ሳሙኤል ተመስገን፣ ትግል ግዛው እና ቴዎድሮስ ምትኩ ጋር በመሆን እየመራው እንደሆነ ሲታወቅ በመስከረም ወር የመጀመሪያ ቀናት የሚደረጉትን የካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ጨዋታዎች ደግሞ ሦሰት ዋና እና ዘጠኝ ረዳት የሀገራችን ዳኞች እንደሚመሩት ተጠቁሟል።

በዚህም መስከረም 1 የደቡብ ሱዳኑ አትባራ እና የሱዳን አል ሃሊ ሜሮዌ የሚያደርጉትን የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ ሊዲያ ታፈሰ የመሐል ዳኛ በመሆን ከረዳቶቿ ሳሙኤል ተመስገን ፣ፋሲካ ብሩ እንዲሁም ለሚ ንጉሴ ጋር በመተባበር እንደምትመራ ታውቋል። ከዚህ ጨዋታ በተጨማሪ በተመሳሳይ ውድድር መስከረም 2 በሱዳኑ ሄይ አልዋዲ በሊቢያው ሃሊ ትሪፖሊ መካከል የሚደረገውን ጨዋታ ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ ከክንዴ ሙሴ፣ ሸዋንግዛው ተባበል እና ብሩክ የማነብርሃን ጋር በመሆን እንደሚመራ ተመላክቷል።

ቅዳሜ መስከረም 1 በአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ የጅቡቲው አስ አርታ ሶላር 7 ከኬኒያው ተስከር ጋር የሚያደርጉትን ጨዋታ ደግሞ ኃይለየሱስ ባዘዘው ከትግል ግዛው፣ ይበቃል ደሳለኝ እና በላይ ታደሰ ጋር በመሆን እንደሚመሩት የካፍን መረጃ ዋቢ አድርጎ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።

ያጋሩ