በኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ውድድር ወደ ግማሽ ፍፃሜ ያለፉ ቡድኖች ታውቀዋል

የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ውድድር የሩብ ፍፃሜ ጨዋታዎች ዛሬ ሲካሄዱ አዳማ ከተማ፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ አርባምንጭ ከተማ እና ሀዋሳ ከተማ ወደ ግማሽ ፍፃሜ ማለፋቸውን አረጋግጠዋል።

በዕለቱ የተካሄዱት አራቱም የሩብ ጨዋታዎች በሙሉ እጅግ ሳቢ የነበረ ሲሆን የኳሱ ፍሰት እና ጎሎቹ የሚቆጠሩበት መንገድ የታዳጊዎች ውድድር ምን ያህል ከፍ ወደ አለ ደረጃ መሻገሩን ያስመለከተ ነበር።

የመጀመርያ ጨዋታ የነበረው የአዲስ አበባ እና የኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ በኢትዮጵያ ቡና አሸናፊነት ተጠናቋል። የመጀመርያዎቹ አስራ አምስት ደቂቃ አዲስ አበባዎች ኳሱን ተረጋግተው እንዳይጫወቱ አፍነው በመያዝ ቡናዎች በፍጥነት ወደ ጎል እየደረሱ ሙከራዎችን ቢያደርጉም ሳይሳካላቸው ቀርቷል። ያም ቢሆን በተደጋጋሚ ያደረጉት ጥረት ተሳክቶላቸው ዮሴፍ በቀለ ባስቆጠረው ጎል ቀዳሚ መሆን ችለዋል። ከጎል ከተቆጠረባቸው በኃላ ብልጫ የወሰዱት አዲስ አበባዎች በሄኖክ ኤርሚያስ አማካኝነት ነፃ የጎል ዕድል አግኝተው ሳይጠቀሙ ቀርተዋል። ኳስን ተቆጣጥረው በፍጥነት ወደ ተቃራኒ ቡድን በመድረስ ይፈጥሩ የነበረውን አጨዋወት በመቀየር ረጃጅም ኳስ መጠቀም የጀመሩት ቡናዎች ከዕረፍት መልስ በድጋሚ በአዲስ አበበ የተወሰደባቸው ብልጫ ቀጥሎ ሙሉቀን በቀለ ከሳጥን ውጭ ባስቆጠራት ግሩም ጎል አንድ አቻ ሆነዋል። በመደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ አንድ አቻ መሆኑን ተከትሎ ወደ መለያ ምት አምርተው ኢትዮጵያ ቡናዎች 7-6 በማሸነፍ ግማሽ ፍፃሜውን ተቀላቅለዋል።

በማስከተል በቀጠለው አዳማ ከተማ ከደቡብ ያገናኘው ጨዋታ ጠንካራ ፉክክር አስመልክቶናል። አዳማ ከተማ እስካሁን ከመጣበት ጥሩ አጨዋወት ዛሬ ተቀዛቅው ሲታዩ ደቡቦች ከክልሉ እግርኳስ ፌዴሬሽን ብዙ ያልተሟላላቸውን ነገሮች ቢኖርም ከነችግሮቻቸው በየጨዋታው እያስደመሙን መጥተው ዛሬም ይህን ጥንካሬያቸውን አስመልክተውናል። ገና በጨዋታው ጅማሬ በፍጥነት ወደ ጎል የደረሱት ደቡቦች ፍፁም ቅጣት ክልል ውስጥ ኳስ በእጅ በመነካቱ የተገኘውን ዕድል ያአብተክል ምናሴ ወደ ጎልነት ቀይሮት መምራት ጀምረዋል። ብዙም ሳይቆይ አብዱልፈታ ከግራ መስመር ተከላካይ በጥሩ ሁኔታ በማለፍ ለሳዲቅ ዳሪ አቀብሎት በቀላሉ ደገፍ በማድረግ አዳማዎችን አቻ አድርጓል።

የመጫወት ፍላጎታቸው ከፍተኛ የነበረው ደቡቦች ከዕረፍት መልስ ጨዋታውን በሚገባ ተቆጣጥረው ማሸነፍ የሚችሉበት ዕድሎችን መፍጠር ቢችሉም አለመጠቀማቸው በመጨረሻ ዋጋ አስከፍሏቸዋል። በተለይ ሚሊዮን ኃይሉ የአዳማ ተከላካዮችን ስህተት ተከትሎ ያገኘውን ኳስ ሁለት ተከላካዮችን አልፎ ከግብጠባቂው ጋር ብቻውን ተገናኝቶ አገባው ሲባል በተጨማሪ ግብጠባቂውን አልፎ በዶ ጎል አግኝቶ የጎሉ መረብ ሲጠበቅ ባላንሱን ስቶ ያመከነው ኳስ የሚያስቆጭ ነበር። ጨዋታው የተለየ ነገር ሳያስመለክተን በመጨረሻም ወደ መለያ ምት አምርቶ አዳማ ከተማ 5-4 በማሸነፍ ወደ ግማሽ ፍፃሜው ማለፉን አረጋግጧል።

በውጤቱን ተከትሎ ደቡቦች ካሳለፉት የባቱ የሰቆቃ ቆይታ አኳያ ተጫዋቾች አሰልጣኞቹን ጨምሮ በሙሉ ሜዳ ውስጥ በሀዘን እንባ ተሞልተው ሲያለቅሱ የተመለከተ እጅግ ልብ ይሰብር ነበር። በዚህ ቡድን ውስጥ በርከት ያሉ አቅም ያላቸው ተጫዋቾችን ብንመለከትም የአንበሉ ሚኪያስ አቅም የተለየ ተስፋ ሰጪ ሆኖ አግኝተነዋል።

የዕለቱ ሦስተኛ ጨዋታ የሆነው እና ድራማዊ በሆነ መንገድ የተጠናቀቀው የአርባምንጭ እና የወላይታ ድቻ ጨዋታ በአርባምንጭ አሸናፊነት ተጠናቋል።

በመጀመርያው አጋማሽ እንደወሰዱት ብልጫ ጎል ማስቆጠር የሚገባቸው ድቻዎች ቅዱስ ቂርቆስ እና ሙሉቀን ዳንኤል አከታትለው ባስቆጠሩት ጎል እስከ ዕረፍት ድረስ መምራት ችለው ነበር።
ድራማዊው ትዕይንት ባስመለከተን የጨዋታው ሁለተኛ ክፍለ ጊዜ አርባምንጮች ድክመታቸውን አርመው በመምጣት ቡድኑን ያነቃቃች ግሩም ጎል በኃይሉ ንጋቱ ከሳጥን ውጭ አስቆጥሮ የጎል መጠኑን መቀነስ ጀመሩ። የአዞዎቹ ወደ ጨዋታው ለመመለስ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ቀጥሎ በዕለቱ ድንቅ እንቅስቃሴ ያስመለከተን ፋሲል ፋንታዬ የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ሁለተኛ ጎል አስቆጥሮ ቡድኑን አቻ አድርጓል። ሁለተኛው ጎል ተቆጥሮባቸው አቻ ከሆኑ በኃላ ከፈዘዙበት ነቃ ያሉት ድቻዎች በድጋሚ መምራት የሚችሉበትን እድል ሙሉቀን አግኝቶ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። 

ጨዋታው በአቻ ውጤት ተጠናቆ ወደ መለያ ምት አመራ ሲባል የዕለቱ ኮከብ ፋሲል ከመስመር የተሻገረለትን ኳስ በሚገርም የግንባር ኳስ ለቡድኑ ሦስተኛ ለራሱ ሁለተኛ ጎል አስቆጥሮ ቡድኑን ከሁለት ለዜሮ ከመራት አሸናፊ እንዲሆኑ አስችሏል።

የመጨረሻ ጨዋታ ሆኖ አመሻሽ ላይ የተጠናቀቀው የሀዋሳ እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ በሀዋሳ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። ወደ ጎል የመድረስ አቅማቸው ጥሩ የሆኑት ፈረሰኞቹ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ሲደርሱ በሚቋረጡ ኳሶች ምክንያት በመጀመርያው አጋማሽ ሁለት ግልፅ የማግባት አጋጣሚ ከሰጥን ውጭ መፍጠር ችለዋል። በአንፃሩ ሀዋሳዎች በጥሩ የመከላከል አደረጃጀት ውስጥ የሚያደርጉት የመልሶ ማጥቃት አጨዋወታቸው ስኬታማ አድርጓቸው ህገአብ ካሳሁን እና ዚያድ ከድር አስቆጥረው ሀዋሳዎች ሁለት ዜሮ መምራት ችለዋል።

 ወደ ጨዋታው ለመመለስ የሚያደርጉት ጥረት ከእንቅስቃሴ ብልጫ ውጭ የጎል ብዙም ዕድል በመፍጠር ያልቻሉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በጨዋታው መጠናቀቂያ አካባቢ በአብርሀም ጫንያለው አማካኝነት ከሽንፈት ያልታደጋቸውን የማስተዛዘኛ ጎል አስቆጥረው ጨዋታው በሀዋሳ አሸናፊነት ተጠናቋል።

የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎች

ቅዳሜ ነሐሴ 29

03:00 ኢትዮጵያ ቡና ከ አርባምንጭ

05:00 ሀዋሳ ከተማ ከአዳማ ከተማ