“… ባደረግነው ማጣራት ተጫዋቾቹ በሆቴሉ እንደሌሉ አወቅን” ውበቱ አባተ

ከዲሲፕሊን ጋር በተያያዘ ከብሔራዊ ቡድኑ የተቀነሱትን አራቱን ተጫዋቾች በተመለከተ አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ገለፃ አድርገዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ከደቂቃዎች በፊት ካሉበት ጋና በበይነ-መረብ የነገውን የጋና ጨዋታ አስመልክቶ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል። አሠልጣኙ ያነሱትን ሙሉ ሀሳብ ከቆይታ በኋላ ይዘን የምንመለስ ሲሆን ቡድኑ ወደ ጋና ሲያመራ በዲሲፕሊን ምክንያት የቀነሳቸውን ተጫዋቾች አስመልክቶ ከጋዜጠኞች ለተነሳላቸው ጥያቄ የሰጡትን ማብራሪያ ለአሁን ይዘን ቀርበናል።

“በመጀመሪያ ደረጃ በብሔራዊ ቡድን ውስጥ ያለ ማንኛውም አባል ሊተገብራቸው የሚገቡ ብለን ያስቀመጥናቸው ነገሮች አሉ። ማንኛውም የቡድኑ አባል በቆይታው ሊያደርገው የሚገባ እና ማድረግ የሌለበትን ነገር ማለት ነው። ሁላችንም አንድ ላይ ካምፕ የተቀመጥነው ለጨዋታው በአካልም ሆነ በአምሮ በተሻለ ደረጃ ለመዘጋጀት ነው። አሁን እንደምታውቁት የኮቪድ-19 ሁኔታ አለ። ከዚህ ጋር ተያይዞ እንቅስቃሴዎች የተገደቡበት ሁኔታ አለ። ከዚህ ውጪ ባህርዳር ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለከተማውም ነዋሪ የሰዓት ገደብ ተጥሏል።

“እንዳልኩት እኛ የራሳችን ህጎችን አስቀምጠናል። እንደ ተሰማው ፍፁም ዓለሙ፣ ዊልያም ሠለሞን፣ በዛብህ መለዮ እና ሱራፌል ዳኛቸው የነበረውን ህግ ተላልፈው ተገኝተዋል። እንደ አጋጣሚ ተጫዋቾቹን ለመቆጣጠር ወይም ለመከታተል ሳይሆን እንደ ማንኛውም ጊዜ የተጫዋቾቹን የግል ብቃት ለማሻሻል እና በዩጋንዳው ጨዋታ ያየነውን ነገር ለማስረጋት ወርደን ውይይት ለማድረግ ፍፁምን ስንፈልገው አጣነው። ከዛ ባደረግነው ማጣራት ስማቸውን የጠቀስኳቸው ተጫዋቾች በሆቴሉ እንደሌሉ አወቅን። ከሆቴሌ ባደረግነው ክትትልም ከፍፁም ውጪ ያሉት ሦስቱ ተጫዋቾች 4:30 ላይ ነው ወደ ሆቴል የገቡት። ፍፁም ደግሞ ከአምስት ሰዓት በኋላ ነው የመጣው። ተጫዋቾቹ ያለ ፍቃድ ነው የወጡት። የት እንደሚሄዱም አልነገሩንም ነበር። ከዚህ መነሻነት ብሔራዊ ቡድኑን እንዲሰናበቱ አድርገናል።” ብለዋል።

አሠልጣኝ ውበቱ አራቱ ተጫዋቾች የተቀመጠውን ህግ ተላልፈው በመገኘታቸው መቀጣታቸውን በሚናገሩበት ጊዜም ተጫዋቾቹ ጥፋታቸውን አምነው ይቅርታ መጠየቃቸውን አያይዘው ጠቁመዋል።