አዲስ አበባ ከተማ ወደ ሌሎች ክለቦች ለማምራት የተስማሙትን ሁለት ነባር ተጫዋቾች ውል አድሷል

ወደ ሊጉ ካሳደጉት አሠልጣኝ እስማኤል አቡበከር ጋር እንደሚቀጥሉ የገለፁት አዲስ አበባ ከተማዎች ከቀናት በፊት ወደ ጅማ አባጅፋር እና ሰበታ ከተማ ለማምራት የተስማሙትን ተጫዋቾቻቸውን ውል ማደሳቸው ታውቋል።

በተጠናቀቀው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ 51 ነጥቦችን በመሰብሰብ ዳግም የሀገሪቱን ከፍተኛ የሊግ እርከን የተቀላቀለው አዲስ አበባ ከተማ ጠንከር ያሉ ግምገማዎችን በውስጥ አሰራሩ ላይ በማድረግ ከሰሞኑን ለ2014 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መዘጋጀት እንደጀመረ መዘገባችን ይታወሳል። ክለቡም ከአሠልጣኝ እስማኤል አቡበከር ጋር እንደሚቀጥል ከገለፀ በኋላ በይፋ በዚህ ሳምንት ወደ ዝውውር ገበያው ገብቷል።

አዲሱ የሊጉ ክለብ አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ ከመቀላቀሉ በፊት በተጠናቀቀው ዓመት ወሳኝ ሚና የነበራቸውን ነባር ተጫዋቾች ውል ማራዘም ጀምሯል። የመጀመሪያው ተጫዋችም የመስመር አጥቂው ፍፁም ጥላሁን ነው። ከኢትዮጵያ ቡና ተስፋ ቡድን የተገኘው ፍፁም በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት አዲስ አበባ ከተማን ተቀላቅሎ መልካም እንቅስቃሴ ማሳየቱ አይዘነጋም። እስከ ጥቅምት 30 ውል የነበረው ተጫዋቹም ከቀናት በፊት ወደ ጅማ አባጅፋር ለማምራት ተስማምቶ የነበረ ቢሆንም በዛሬው ዕለት በመዲናው ክለብ ለመቆየት በመወሰን ፊርማውን ለአንድ ዓመት ማኑሮ ተረጋግጧል።

እንደ ፍፁም ሁሉ አዲስ አበባ ከተማን ለቆ ወደ ሌላኛው የሊጉ ክለብ (ሰበታ ከተማ) ለማምራት ከቀናቶች በፊት ተስማምቶ የነበረው ብዙዓየሁ ሰይፉም በዛሬው ዕለት የአንድ ዓመት ውል በክለቡ መፈረሙ ታውቋል። የቀድሞ የሀላባ ከተማ አማካይ በተመሳሳይ ዘንድሮ አዲስ አበባ ከተማን ተቀላቅሎ ጥሩ ብቃት ሲያሳይ መቆየቱ አይረሳም። እንደተገለፀው ወደ ሰበታ ከተማ ለማምራት ስምምነት ፈፅሞ የነበረ ቢሆንም በአዲስ አበባ ከተማ አሠልጣኞች እና አመራሮች ድርድር ዳግም በክለቡ ለመቆየት በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ቢሮ ተገኝቶ ውሉን አድሷል።

ያጋሩ