ቡናማዎቹ ወደ ዩጋንዳ ጉዞ ጀምረዋል

ከ2004 በኋላ ዳግም ወደ አፍሪካ ምድረክ ብቅ ያሉት ኢትዮጵያ ቡናዎች ከደቂቃ በፊት በሁለተኛ ምዕራፍ ወደ ዩጋንዳ ጉዞ ሲጀምሩ ጨዋታውን በግብ ጠባቂ አሰልጣኝ እየተመሩ ያደርጋሉ።

ቡናማዎቹ የፊታችን እሁድ በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ቅድመ ማጣርያ ጨዋታቸውን ከዩጋንዳው ዩ አር ኤን የሚያደርጉ ሲሆን በትናትናው ዕለት የቡድኑ ሥራ አስኪያጅ አቶ ገዛኸኝ ወልዴ አቅንተው ነበር። ዛሬ ደግሞ ሁለተኛ ምዕራፍ ተጓዥ የቡድኑ አባላት እና ደጋፊዎችን ጨምሮ በጥቅሉ ሠላሳ ስድስት የሚሆኑ ከደቂቃዎች በፊት ወደ ዩጋንዳ ጉዞ ጀምረዋል። ከሁለት ሰዓት የአየር በረራ በኃላ ኢንቴቤ አየር ማረፊያ የሚደርሱት ቡናዎች በማስከተል የ25 ኪሎ ሜትር የመኪና ጉዞ ካደረጉ በኃላ ካምፓላ በመድረስ በተያዘላቸው ሆቴል የሚያርፉ ይሆናል።

ከቡድኑ ጋር አብሮ እንደሚጓዝ ስሙ ተገልፆ የነበረው አዲስ ፈራሚው ነስረዲን ኃይሉ ከጉዳቱ ሙሉ ለሙሉ ባለማገገሙ የማይጓዝ መሆኑ ሲታወቅ በምትኩ ናትናኤል በርሄ አሁን ወደ ስፍራው ካቀኑት አባላት ውስጥ ተካቷል።

አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ከላይሰንስ ጋር ተያይዞ ቡድናቸውን በቴክኒክ ቦታ ላይ የማይመሩ በመሆናቸው በምትኩ የሴቶች ቡድን አሰልጣኝ የሆኑትን አሰልጣኝ ሀብተወልድን ለማድረግ ከካፍ ጋር ንግግር ተጀምሮ የነበረ ቢሆንም በካፍ ዘንድ ተቀባይነት አላገኘም። ይህን ተከትሎ የግብጠባቂ አሰልጣኙ ፀጋዘአብ አስገዶም ቡድኑን እንዲመራ ካፍ እውቅና በመስጠቱ የደርሶ መልስ ጨዋታውን በፀጋዘዓብ የሚከወን ይሆናል።

ሦስተኛው ምዕራፍ ተጓዥች በደጋፊ ማህበሩ አቶ ክፍሌ አማረ እየተመሩ አስራ አምስት የሚጠጉ ደጋፊዎች ነገ ረፋድ ላይ ወደ ስፍራው የሚያቀኑ ሲሆን ቁጥራቸው የማይታወቅ ከኬንያ ከደቡብ አፍሪካ የሚገኙ የኢትዮጵያ ቡና የልብ ደጋፊዎች ካሉበት ሀገር ወደ ዩጋንዳ እንደሚመጡ ሰምተናል።

ኢትዮጵያ ቡና የመጀመርያ ጨዋታውን የፊታችን እሁድ በሴይንት ሜሪ ስታዲየም (ሰው ሰራሽ ሜዳ) 10:00 ላይ የሚያደርጉ ይሆናል። ጨዋታውንም የሚመሩት አራቱም ዳኞች ከታንዛኒያ ሲሆን የጨዋታው ኮሚሽነር ሩዋንዳ መሆናቸው ታውቋል።