“ከጠበቅነው በላይ ስላሳያችሁን እጅግ እናመሰግናለን” ክብርት ወ/ሮ አዳነች አበቤ

የከፍተኛ ሊጉ ምድብ ለ በበላይነት በማጠናቀቅ ወደ ፕሪምየር የሊግ የተቀላቀለው አዲስ አበባ ከተማ በመዲናው መስተዳደር ሽልማት ተበርክቶለታል።

በሀያት ሪጀንሲ ሆቴል በተካሄደው የዕውቅና ምሽት የከተማዋ ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አበቤ የአአ የስፖርት ኮሚሽን ኮሚሺነር በላይ ደጀን እና የካቢኔ አባላት ጥሪ የተደረገላቸው የክብር እንግዶች በተገኙበት መርሐግብሩ ተካሄዷል። የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር በማድረግ መድረኩን የከፈቱት የአአ የስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ በላይ ደጀን አጠር ያለ ንግግር በማድረግ ክለቡ ዳግም ወደ ፕሪምየር ሊጉ በማደጉ ከፍተኛ ድጋፍ ላደረጉ አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ቡድኑ በውድድር ዓመቱ ያሳካቸውን ዋንጫዎችም ለክብርት ከንቲባዋ አበርክተዋል።

በማስከተል ካለው የሰዓት መጣበብ አንፃር በቀጥታ ወደ ሽልማት አሰጣጥ የተኬደ ሲሆን ክብርት ወ/ሮ አዳነች አበቤ የተዘጋጁትን ሽልማቶች ለቡድኑ አባላት በየደረጃው ከሸለሙ በኃላ የመዝግያ ንግግር አድርገዋል። በንግራቸውም ” ባደረጋችሁት ከፍተኛ ጥረት ከምድባቹሁ አንደኛ ሆናቹሁ በማጠናቅ ከተማችንን ሰም በማስጠራታቹሁ ከጠበቅነው በላይ ስላሳያችሁን እጅግ እናመሰግናለን።ጠአዲስ አበባ እግርኳስ የሚወደድባት ከተማ ናት። ከተማዋን የሚመጥን ደረጃ ትልቅነቷን የሚገልፅ ክለብ እንዲኖራት ስንፈልግ ስንጥር ቆይተናል። ይህ እናንተ ያስመዘገባችሁት ውጤት ትልቅ ተስፋ ሰጥቶናል። ስለዚህ ጥረታቹሁ ጎልቶ ይወጣ ዘንድ በቀጣይ ውጤታማ እንድትሆኑ የከተማው አስተዳደር ሁልጊዜ ከጎናቹሁ ይቆማል። ይህንንም ላረጋግጥላቹሁ እፈልጋለው።” ብለዋል።

በመቀጠል በየደረጃው  በተሰጠው ሽልማት መሠረት:-

* አሰልጣኝ እስማኤል አቡበከር – የሁለት መቶ ሺህ ብር ተሸላሚ

* የግብጠባቂዎች አሰልጣኙን ጨምሮ ለረዳቶቹ – ለእያንዳንዳዳቸው መቶ ሀምሳ ሺህ

* ለሁለት ለህክምና ባለሙያዎች – ለእያንዳንዳቸው ስልሳ ሺህ ብር

* በአመራር ሰጪነት የክለቡ ስራ አስኪያጅ እና ፕሬዝደንት – ለእያንዳንዳቸው ዘጠና ሺህ ብር

* አንደኛ ዕርከን ተሸላሚ ለሆኑ አስራ ስምንት ተጫዋቾች – ለእያንዳንዳቸው መቶ ሀምሳ ሺህ ብር

* ሁለተኛ ዕርከን ተሸለሚ ለሆኑ ሰባት ተጫዋቾች – ለእያንዳንዳቸው መቶ ሺህ ብር

* በቢጫ ቲሴራ በመጫወት ቡድኑን ላገለገሉ አራት ወጣት ተጫዋቾች – ለእያንዳንዳቸው አርባ ሺህ ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

ከዚህ ውጭ በተለያዩ ተግባራት ክለቡን ላገለገሉ አካላት የገንዘብ እና የዕውቅና ሰርተፍኬት የተበረከተ ሲሆን በአጠቃላይ የከተማው አስተዳደር አምስት ሚሊዮን ብር በላይ ለሽልማቱ ገንዘብ አውጥቷል።