የዋልያዎቹ አሠልጣኝ ውበቱ አባተ የነገው የጋና ጨዋታን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል

👉”ፍፁም ዓለሙ፣ ዊልያም ሰለሞን፣ በዛብህ መለዮ እና ሱራፌል ዳኛቸው የነበረውን ህግ ተላልፈው ተገኝተዋል”

👉”ከጉዳት ጋር ተያይዞ መጠነኛ ጉዳት የነበረባቸው ተጫዋቾች ነበሩ…”

👉”ተጫዋቾቹ ከእንደዚህ አይነት ፍራቻ ወጥተው በጥሩ የራስ መተማመን ያላቸውን ነገር በነፃነት እንዲያሳዩ እየሰራን ነው”

👉”…ነገም መልካም ነገር ይገጥመናል ብዬ አስባለሁ”

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ኳታር ለምታስተናግደው የዓለም ዋንጫ ለማለፍ ከጋና፣ ደቡብ አፍሪካ እና ዚምባቡዌ ጋር የማጣሪያ ጨዋታ ለማከናወን እንደተደለደለ ይታወቃል። ብሔራዊ ቡድኑም ከነገ ጀምሮ ለሚጠብቁት የምድብ የማጣሪያ ጨዋታዎች ከነሐሴ 4 ጀምሮ አዳማ ላይ ዝግጅቱን በማድረግ ባሳለፍነው ሳምንት ወደ ባህር ዳር አቅንቶ ከሴራሊዮን እና ዩጋንዳ ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታ አድርጓል። ከሁለት ቀናት በፊትም የምድብ የመጀመሪያ ጨዋታውን ለማድረግ 23 ተጫዋቾችን በመያዝ ስብስቡ ወደ ጋና አምርቷል።

ዛሬ አመሻሽ በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አዘጋጅነት በበይነ-መረብ የዙም መተግበሪያ አሁን ከሚገኙበት ጋና ኤልማና ከተማ መግለጫ የሰጡት አሠልጣኝ ውበቱ አባተም ስብስባቸው ስላለበት አሁናዊ ሁኔታ እና ስለነገው ወሳኝ ፍልሚያ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ሰጥተዋል።

“በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ከጋና እና ዚምባቡዌ ጋር ላለብን ጨዋታ ከነሐሴ 4 ጀምሮ ዝግጅት ማድረግ ጀምረን ነበር። አዳማ ላይ የተወሰኑ የልምምድ ጊዜያትን ካሳለፍን በኋላ ደግሞ 2 የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎችን ወደ ባህር ዳር ተጉዘን ከሴራሊዮን እና ዩጋንዳ ጋር አድርገናል። ወደ ጋና ከመምጣታችን በፊት ከያዝናቸው አጠቃላይ ተጫዋቾች አምስቱን ቀንሰን 23 ተጫዋቾችን ይዘን ተጉዘናል።

“ከአዲስ አበባ ጠዋት ተነስተን ጋና ምሳ ሰዓት አካባቢ ከደረስን በኋላ የመኪና ጉዞ አድርገን ጨዋታው ወደሚደረግበት ከተማ የደረስነው ምሽት ላይ ነው። ከጉዞ ጋርም ተያይዞ በገባንበት ቀን ልምምድ አልሰራንም። ከዚህ በተረፈ ያለንበት ነገር በጣም ጥሩ ነው። ስብስቡም በጥሩ የሥነ ልቦና ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው።” ብለዋል።

ከአጭሩ የዋልያዎቹ ዋና አሠልጣኝ ገለፃ በኋላ መግለጫውን ለመከታተል የተገኙት በጣት የሚቆጠሩ የብዙሃን መገናኛ አባላት ጥያቄዎችን ማንሳት ጀምረዋል። በቅድሚያም አሠልጣኙ ከዲሲፕሊን ጋር ተያይዞ የቀነሷቸውን ተጫዋቾች በግልፅ እንዲያብራሩ ጥያቄ ተነስቶላቸው ምላሽ ሰጥተዋል።

“በመጀመሪያ ደረጃ በብሔራዊ ቡድን ውስጥ ያለ ማንኛውም አባል ሊተገብራቸው የሚገቡ ብለን ያስቀመጥናቸው ነገሮች አሉ። ማንኛውም የቡድኑ አባል በቆይታው ሊያደርገው የሚገባ እና ማድረግ የሌለበትን ነገር ማለት ነው። ሁላችንም አንድ ላይ ካምፕ የተቀመጥነው ለጨዋታው በአካልም ሆነ በአምሮ በተሻለ ደረጃ ለመዘጋጀት ነው። አሁን እንደምታውቁት የኮቪድ-19 ሁኔታ አለ። ከዚህ ጋር ተያይዞ እንቅስቃሴዎች የተገደቡበት ሁኔታ አለ። ከዚህ ውጪ ባህርዳር ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለከተማውም ነዋሪ የሰዓት ገደብ ተጥሏል።

“እንዳልኩት እኛ የራሳችን ህጎችን አስቀምጠናል። እንደ ተሰማው ፍፁም ዓለሙ፣ ዊልያም ሠለሞን፣ በዛብህ መለዮ እና ሱራፌል ዳኛቸው የነበረውን ህግ ተላልፈው ተገኝተዋል። እንደ አጋጣሚ ተጫዋቾቹን ለመቆጣጠር ወይም ለመከታተል ሳይሆን እንደ ማንኛውም ጊዜ የተጫዋቾቹን የግል ብቃት ለማሻሻል እና በዩጋንዳው ጨዋታ ያየነውን ነገር ለማስረጋት ወርደን ውይይት ለማድረግ ፍፁምን ስንፈልገው አጣነው። ከዛ ባደረግነው ማጣራት ስማቸውን የጠቀስኳቸው ተጫዋቾች በሆቴሉ እንደሌሉ አወቅን። ከሆቴሌ ባደረግነው ክትትልም ከፍፁም ውጪ ያሉት ሦስቱ ተጫዋቾች 4:30 ላይ ነው ወደ ሆቴል የገቡት። ፍፁም ደግሞ ከአምስት ሰዓት በኋላ ነው የመጣው። ተጫዋቾቹ ያለ ፍቃድ ነው የወጡት። የት እንደሚሄዱም አልነገሩንም ነበር። ከዚህ መነሻነት ብሔራዊ ቡድኑን እንዲሰናበቱ አድርገናል።”

በተያያዘ ከዚህ ቀደም በክለብ ደረጃ የተቀጡ ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ መጥራታቸውን ተከትሎ የሚጋጭ ነገር የለም ወይ ተብሎ ለተነሳላቸው ተከታይ ጥያቄም አሠልጣኙ “ልክ ነው አስቻለው ታመነ እና ጌታነህ ከበደ በቅዱስ ጊዮርጊስ ቅጣት ተጥሎባቸው ነበር። ተጫዋቾቹ ቅጣታቸውን በክለባቸው በኩል ተወጥተዋል። ያጠፉትን ጥፋት እኔ ለማጣራት ሞክሬ ነበር። ግን ምንም የደረሰኝ ነገር የለም። ክለቡ የወሰነውን ውሳኔ በግሌ አከብራለው። ግን ተጫዋቾቹ እኛ ጋር ባላቸው ቆይታ በቡድኑ ያለውን ነገር አክብረው ነው እየቀጠሉ ያሉት። ክለባቸው ቅዱስ ጊዮርጊስ ስለሆነ ወይም የቡድኑ አንጋፋ ተጫዋቾች ስለሆኑ ምንም ያደረግነው ነገር የለም። ስለዚህ እኛ የምናስቀምጠው ነገር ሁሉንም የሚገዛ ህግ ነው። ግን እኛ ቤት ያለው እና ሌላው ቤት ያለው ህግ የተለያየ ነው። ወደፊትም ተጫዋቾች በክለቦቻቸው የሚያጠፉት ነገር በብሔራዊ ቡድን ህብረት ላይ ተፅዕኖ የሚያመጣ ከሆነ እና መጥፎ አርአያ የሚሆን ከሆነ ግን ክለቦቹ የወሰዱትን እርምጃ እኛ የማንከተልበት ምንም ምክንያት የለም።” ብለው መልሰዋል።

በተከታይነት ስብስቡ ስላለበት አሁናዊ ሁኔታ እና የጉዳት ጉዳዮችን በተመለከተ አሠልጣኙ ጥያቄ ቀርቦላቸዋል።

“ጨዋታውን የምናደርግበት ከተማ ከአክራ 150 ኪሎ ሜትሮችን ትርቃለች። ከተማው ሞቃታማ አየር ነው ያለው። መጠነኛ ወበቅም አለ። ግን ምሽት ላይ ነው ጨዋታችን። ምንም እንኳን እንደ ሀገር ቤት ባይሆንም በአንፃራዊነት ቀን ከመጫወት ምሽት ላይ መጫወታችን ይሻላል።

“ከጉዳት ጋር ተያይዞ መጠነኛ ጉዳት የነበረባቸው ተጫዋቾች ነበሩ። አሁን ግን የተጎዱት ተጫዋቾች አገግመዋል። ስለዚህ ሀያ ሦስቱም ተጫዋቾች በመልካም ጤንነት ላይ ይገኛሉ።

የጥያቄ እና መልስ መርሐ-ግብሩ ቀጥሎ ስለ ነገው ተጋጣሚ ጋና የተጠየቁት አሠልጣኙ ተከታዩን ሰፊ ማብራሪያ ከዚህ ቀደም ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር ስንጫወት ከገጠመው ውጤት ጋር እያነፃፀሩ እንዲሁም ከቡድኑ እድገት ጋር እያመሳከሩ ሀሳብ ሰጥተዋል።

“የምድብ ድልድላችን ከታወቀ ጀምሮ በምድባችን የሚገኙ ብሔራዊ ቡድኖችን ለመመልከት ጥረናል። ሁሉም ቡድኖች ከእኛ ተጫዋቾች የተሻለ ልምድ እና የተጫዋቾች ጥራት ያላቸው ናቸው። የጋና ብሔራዊ ቡድንም ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን ነው። በተቻለን መጠንም የቡድኑን አጨዋወት ለመመልከት ሞክረናል።

“ከዚህ በፊት ከጋና ጋር ባደረግናቸው ጨዋታዎች ጥሩ ታሪክ የለንም። ይህንን እያሰቡ መጫወት በጣም ከባድ ነው የሚሆነው። በምንም መልኩ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ እየመጣ እንደሆነ ሁሉም ሰው ያውቃል። ሎተሪ ካልሆነ በስተቀር ማንም ትልቅ ነገር ላይ በአንዴ አይመጣም። ሁሉም ነገር የሂደት ውጤት ነው። ከዚህ በፊት የነበሩብንን ክፍተቶች እያሻሻልን ለውጥ የማናመጣበት ምንም ምክንያት የለም። ነገም መልካም ነገር ይገጥመናል ብዬ አስባለሁ። ተጫዋቾቹ ከእንደዚህ አይነት ፍራቻ ወጥተው በጥሩ የራስ መተማመን ያላቸውን ነገር በነፃነት እንዲያሳዩ እየሰራን ነው።

“በአጠቃላይ ምድባችን ላይ ያሉት ጠንካራ ብሔራዊ ቡድኖች ናቸው። እኛ ወደ እዚህ ቦታ ስንመጣ በፊፋ ደረጃ 147ኛ ላይ ነበርን። አሁን ወደ 137ኛ ከፍ ብለናል። ይህ ቢሆንም አሁን ላይ እኛ ሳንሆን ከእነዚህ ቡድኖች ጋር በደረሰን የምንለው ትላልቆቹ ናቸው ከእኛ ጋር በደረሰን ብለው የሚመኙት። በዚህ ምድብም ዚምባቡዌ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ጋና ከእኛ በላይ የሚገኙ ጠንካሮች ናቸው። ግን ያለንን ልዩነት የሚያጠብ ነገር ለመስራት እየሞከርን ነው። አሁን ላይ መታየት ያለበትም ሂደቱ ነው።

“በዩጋንዳው ጨዋታ የተሻለ ያየነው ነገር አለ። ጨዋታው ላይም ቡድኑ እድገት እያሳየ እንደሆነ በደንብ ታይቶበታል። ከኮቪድ መልስ ከዛምቢያ ጋር ከተጫወትንበት ጊዜ ጀምሮ ቡድኑ እድገት እያሳየ ነው። ውጤቶቹም ሆነ እንቅስቃሴዎቹ ይሄንን ነው የሚያሳዩት። እርግጥ ብዙ የሚታረም ነገር አለ። ግን በአንፃራዊነት በብዙ ነገሮች እያደግን ነው። ለአሁኑ የጋና ጨዋታ ግን እንደ ዩጋንዳው ጨዋታ እንቀሳቀሳለን የሚል ሙሉ እምነት የለንም።” ብለዋል

በመጨረሻ በነገው ፍልሚያ ቡድኑ የሚከተለውን የጨዋታ መንገድ በመተመለከተ አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ከሚታወቁበት ነገር እንደማይወጡ ከወጡ ግን ለተጋጣሚ ቡድን ምቹ ነገር እንደሚፈጠር እና ከአሰላለፍ ጋርም ተያይዞ ብዙም ለውጦች እንደማይኖሩ ጠቅሰው በመከላከል አደረጃጀት ላይ ግን ጠንካራ ነገር እንደሚኖር አመላክተው መግለጫውን አገባደዋል።

ያጋሩ