ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከከፍተኛ የጨዋታ ብልጫ ጋር የደቡብ ሱዳኑን ዪ ጆይንት ስታርስን 10-0 በማሸነፍ ምድቡን በበላይነት አጠናቋል።
የመጨረሻ የምድብ ጨዋታቸውን ለማድረግ ወደ ሜዳ የገቡት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች 10-1 ካሸነፉበት አሰላለፍ ስድስት ለውጦች አድርገዋል። በዚህም አሠልጣኝ ብርሃኑ ግዛው ግብ ጠባቂዋ ንግስት መዓዛን ጨምሮ ታሪኳ ዴቢሶ፣ ትዕግስት ኃይሌ፣ ትዕግስት ያደታ፣ እመቤት አዲሱ፣ ፀጋነሽ ወራና ወደ አሰላለፉ ሲያመጡ ታሪኳ በርገና፣ ትዝታ ኃይለሚካኤል፣ ብዙዓየሁ ታደሰ፣ ሰናይት ቦጋለ፣ የምስራች ላቀው፣ አረጋሽ ካልሳ ደግሞ እንዲያርፉ ተደርጓል።
በጨዋታው ጅማሮ ላይ ወደ ግብ በመድረሱ ረገድ ተሽለው የተገኙት ዬ ጆይንት ስታርሶች ገና በጊዜ መሪ ለመሆን አከታትለው ሙከራዎችን አድርገው ነበር። በተለይ በአራተኛው ደቂቃ የባንክ ተጫዋቾች የሰሩትን ስህተት ተጠቅማ ማኩንጋ ጆሴፍ የሰላ ሙከራ አድርጋ ነበር። ቀስ በቀስ እየተሻሻሉ የመጡት ባንኮች በበኩላቸው ከደቂቃ በኋላ ከመዓዘን ምት መነሻን ያደረገ ኳስ ከቀኝ መስመር ሲሻማ ባገኘችው ሎዛ የግንባር ኳስ የመጀመሪያ ጥቃታቸውን ፈፅመዋል። በስምንተኛው ደቂቃ ደግሞ መሪ የሆኑበትን ጎል አግኝተዋል። በዚህም ከቀኝ መስመር ከተከላካዮች አፈትልካ የወጣችው መዲና ዐወል ፍጥነቷን እና ከኳስ ጋር ያላትን ምቾት በግልፅ ያሳየችበትን ጎል መረብ ላይ አሳርፋለች።
ጨዋታው ሩብ ሰዓት ላይ ሲደርስ ደግሞ ሌላኛዋ የቡድኑ አጥቂ ሎዛ አበራ በተመሳሳይ ከተከላካዮች አፈትልካ በመውጣት ከግብ ጠባቂው ናዋላ ማጆክ ጋር አንድ ለአንድ በመገናኘት ኳስ እና መረብን በማሳረፍ የባንክን መሪነት አሳድጋለች። ከአምስት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ የመጀመሪያውን ጎል ያስቆጠረችው መዲና ሌላ ጥሩ ኳስ ወደ ግብ ልካ መክኖባታል። በተጠቀሰው ደቂቃ ጥሩ ሙከራ የሰነዘረችው መዲና በ25ኛው ደቂቃ ከግራ መስመር ያገኘችውን ኳስ እየገፋች በመሄድ ለቡድኗ አምበል በማቀበል ሎዛ አበራ ለራሷ ሁለተኛ ለቡድኗ ሦስተኛ ጎል አስቆጥራለች።
እንደ አጀማመራቸው መዝለቅ ያልቻሉት ጆይንት ስታርሶች የባንክን ጫና መቋቋም ተስኗቸው ታይቷል። በ29ኛው ደቂቃ ግን እምብዛም ሥራ ያልበዛባትን የባንክ ግብ ጠባቂ ንግስቲ መዓዛን ለመፈተን ጥረው ነበር። በዚህም ኪሊጋ ሎኮንጋ ከተከላካዮች ጋር ታግላ ያገኘችውን ኳስ ወደ ግብነት ለመቀየር ብትመታውም ኳሱ የግቡን አግዳሚ ጨርፎ ወደ ውጪ ወጥቷል። የሀይል ሚዛኑን ወደ ራሳቸው አድርገው መጫወት የቀጠሉት የአሠልጣኝ ብርሃኑ ግዛው ተጫዋቾች በተከታታይ ግቦችን ማስቆጠር ቀጥለዋል። በቅድሚያም በ32ኛው ደቂቃ ፀጋነሽ ከቀኝ መስመር ያሻገረችውን ኳስ ራሷን ነፃ አድርጋ ኳስ ስትጠብቅ የነበረው ሎዛ አግኝታው በቀላሉ ግብ ስታደርገው ከደቂቃ በኋላ ደግሞ ይህንን ኳስ አመቻችታ የሰጠችው ፀጋነሽ ከሳጥኑ ውጪ ሆኖ ከሎዛ የተቀበለችቅን ኳስ እጅግ ድንቅ በሆነ አመታት ወደ ግብ ልካው ለቡድኗ አምስተኛ ጎል አስቆጥራለች።
ግብ ማስቆጠር ያልደከማቸው የባንክ ተጫዋቾች በ35 እና 37ኛው ደቂቃም ተጨማሪ ግቦችን አስቆጥረዋል። በ35ኛው ደቂቃ ተከላካዮችን አምልጣ የወጣችው ሎዛ ለመዲና ያመቻቸችላትን ኳስ ፈጣኗ አጥቂ ደርሳ ለቡድኗ ስድስተኛ ጎል አድርጋዋለች። ድንቅ ጥምረት በጨዋታው እያሳዩ የሚገኙት መዲና እና ሎዛ በ37ኛው ደቂቃም ሌላ የተጣመሩበትን አጋጣሚ ተመልክተናል። በዚህም መዲና ከወደ ግራ መስመር ያገኘችውን ኳስ ለሎዛ አቀብላት አምበሏ ግብ አስቆጥራለች። የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 7-0 መሪነት ተጠናቆ ተጫዋቾች ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
ተጫዋቾቻቸውን አፈራርቆ ለመጠቀም ለውጦችን በማድረግ ሁለተኛውን አጋማሽ የቀረቡት አሠልጣኝ ብርሃኑ ግዛው ቡድናቸው በመጀመሪያው አጋማሽ የነበረውን ጫና ጋብ አድርጎ ሲጫወት ታይቷል። እርግጥ በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ፀጋነሽ ሁለት ሙከራዎችን አድርጋ የነበረ ቢሆንም ቡድኑ ግብ ሳያገኝ 59ኛው ደቂቃ ደርሷል። በዚህ ደቂቃ ሎዛ አበራ ራሷ ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን የቅጣት ምት በጥሩ ሁኔታ ወደ ግብነት ቀይራ የቡድኗን መሪነት ወደ ስምንት ከፍ አድርጋለች።
ጨዋታው ቀጥሎ 65ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ግብ ያልበቃው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዘጠነኛ ጎል አስመዝግቧል። በዚህም ሁለተኛው አጋማሽ ከተጀመረ ሁለት ጥሩ ጥሩ ዕድሎችን የፈጠረችው ፀጋነሽ በሦስተኛው አጋጣሚ ሌላ ድንቅ ጎል የግብ ዘቧ ናዋላ ማጆክን አልፋ አስቆጥራለች። ከአስራ ሦስት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ሎዛ መዲና ከቀኝ መስመር ያሻገረችላትን ኳስ በግንባሯ ወደ ግብነት ቀይራ የጨዋታ የማሳረጊያ ጎል አግኝታለች። ጨዋታውም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 10-0 አሸናፊነት ፍፃሜውን አግኝቷል።
ውጤቱን ተከትሎ ወደ ግማሽ ፍፃሜው ማለፉን ቀድሞ ያረጋገጠው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ምድቡን በበላይነት ማጠናቀቁ እርግጥ ሆኗል። በዚሁ ምድብ የሚገኙት ቪሂጋ ኩዊንስ እና ኒው ጄኔሬሽንስ ያደረጉት ጨዋታ በኬንያው ክለብ ቪሂጋ ኩዊንስ 8-0 አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ የውድድሩ አስተናጋጅ ክለብ ባንክን ተከትሎ ግማሽ ፍፃሜውን ተቀላቅሏል።