የግብ ጠባቂ ስህተት ጋናን ባለ ድል አድርጓል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን በዓለም ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታ ያስተናገደው የጋና ብሔራዊ ቡድን 1-0 በሆነ ውጤት አሸንፏል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ተክለማርያም ሻንቆ፣ አሥራት ቱንጆ፣ ያሬድ ባየህ፣ አስቻለው ታመነ፣ ረመዳን የሱፍ፣ ይሁን እንደሻው፣ ታፈሰ ሰለሞን፣ ሽመልስ በቀለ፣ አቡበከር ናስር፣ ጌታነህ ከበደ እና አማኑኤል ገብረሚካኤልን በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ በማስገባት ጨዋታውን ቀርበዋል።

ኳሱን በተሻለ በመቆጣጠር ጨዋታውን የጀመሩት ዋልያዎቹ ምንም እንኳን እስከ 31ኛው ደቂቃ ድረስ ሙከራ ባያደርጉም ጨዋታውም ለመቆጣጠር ሲጥሩ ነበር። በተቃራኒው ጋናዎች ደግሞ ፈጣን የመስመር ላይ ሽግግሮችን በማድረግ ጫና መፍጠር ይዘዋል። ቡድኑም በ8ኛው ደቂቃ ረመዳን የሰራውን ጥፋት ተከትሎ ያገኘውን የቅጣት ምት በሙባረክ ዋካሶ አማካኝነት ወደ ግብ መትቶት የጨዋታውን የመጀመሪያ ሙከራ ሰንዝሯል። ከስድስት ደቂቃዎች በኋላም በተመሳሳይ ያሬድ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን ሌላ የቅጣት ምት ቡድኑ በአንድሬ አይው አማካኝነት ወደ ግብነት ለመቀየር ቢጥርም ጥፋቱን ማረሚያ ጊዜ ያገኘው የመሐል ተከላካይ ኳሷን በግንባሩ አምክኗታል።

ቀስ በቀስ በኢትዮጵያ ተጫዋቾች የተወሰደባቸውን የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በእጃቸው ማስገባት የጀመሩት ጋናዎች በ25ኛው ደቂቃ መሪ ለመሆን እጅግ ቀርበው ነበር። በዚህም ባባ ራህማን ይሁን እንዳሻው እና አስራት ቱንጆ ሳይግባቡ ቀርተው ያገኘውን ኳስ ወደ ግብነት ሊቀይረው ጥሮ መክኖበታል። ከላይ እንደተጠቀሰው እስከ ግማሽ ሰዓት ድረስ አንድም ሙከራ ያላደረገው ነገርግን ጨዋታውን በመቆጣጠሩ ረገድ ጥሩ የነበረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በ31ኛው ደቂቃ ረመዳን የሱፍ ከግራ መስመር ወደ ግብ በላከው ኳስ ግብ ጠባቂው ኦፎሪ ሪቻርድን ፈትኗል።

35ኛው ደቂቃ ላይ ሙባረክ ዋካሶ ከአንዲ ይያዶም የደረሰውን ኳስ ከሳጥን ውጪ አክርሮ ሲመታው የዋልያዎቹ የግብ ዘብ ተክለማርያም ሻንቆ መቆጣጠር ተስኖት ኳሷ በእግሮቹ መሐል ሾልካ ከመረብ በመዋሀድ ጋና መምራት ጀምራለች። ለተቆጠረባቸው ጎል ፈጣን ምላሽ ለመስጣት ያሰቡ የሚመስሉት የአሠልጣኝ ውበቱ ተጫዋቾች ግብ ካስተናገዱ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ አቡበከር ላይ የተሰራን ጥፋት ተከትሎ ያገኙትን የቅጣት ምት በጌታነህ አማካኝነት ወደ ግብነት ለመቀየር ጥረው ነበር። ነገርግን ግብ ጠባቂው ኦፎሪ ሪቻርድን ኳሱን በቀላሉ ተቆጣጥሮታል። በቀሪ የአጋማሹ ደቂቃዎች ተጨማሪ ሙከራ ሳይታይ ተጫዋቾች ለእረፍት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

በግል ስህተቱ ግብ የተቆጠረበትን የግብ ዘብ ተክለማርያም ሻንቆን በፋሲል ገብረሚካኤል እንዲሁም አማካዩ ታፈሰ ሠለሞንን በመስዑድ መሐመድ ለውጠው ሁለተኛውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የጀመሩት ዋልያዎቹ በ50ኛው ደቂቃ እጅግ ወደ ግብ ቀርበው የነበረ ቢሆንም አጋጣሚውን ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። ጋናዎች ደግሞ ቀደም ብለው ገና አጋማሹ በተጀመረ በሦስተኛው ደቂቃ ጆርዳን አይው በሞከረው የሰላ የቅጣት ምት መሪነታቸውን ሊያሰፉ ነበር።

በ57ኛው ደቂቃ በጥሩ የኳስ ቅብብል ወደ ጋና የግብ ክልል የደረሱት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች በሽመልስ አማካኝነት ጥሩ ጥቃት ፈፅመው አቻ ለመሆን ሞክረው ወጥቶባቸዋል። ጨዋታው ቀጥሎ 72ኛው ደቂቃ ላይ ይቦሃ ያው ተቀይሮ በገባ በመጀመሪያ የኳስ ንክኪው እጅግ ጥብቅ ኳስ ከሳጥን ውጪ ወደ ግብ መትቶ ነበር። ነገርግን ኳሱን ፋሲል በጥሩ ቅልጥፍና መልሶታል። የተመለሰውን ኳስ አንድሬ አይው በድጋሜ ሲመታውም በጥሩ የጊዜ አጠባበቅ ግቡን ላለማስደፈር ሲሞክር የነበረው ፋሲል አክሽፎታል።

በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃዎች ላይ አንድ ነጥብ ይዞ ለመውጣት የታተሩት ተጋባዦቹ የልፋታቸውን ፍሬ ሊያገኙ ነበር። በዚህም በ84ኛው ደቂቃ ተቀይሮ የገባው ሽመክት ጉግሳ ከአቡበከር የተቀበለውን ኳስ ወደ ግብ በቀጥታ መትቶት ቡድኑ አቻ ሊሆን የነበረ ቢሆንም ግብ ጠባቂው እና ተከላካዮች ተረባርበው ኳሱን አውጥተውታል። በቀሪ ደቂቃዎችም ቡድኑ ኳስ እና መረብን ለማገናኘት ቢጥርም ሳይሳካለት ቀርቷል። ጨዋታውም በባለሜዳዎቹ አንድ ለባዶ አሸናፊነት ተጠናቋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የፊታችን ማክሰኞ ባህር ዳር ላይ ከዚምባቡዌ ጋር የጋና ብሔራዊ ቡድን ደግሞ ጆሀንስበርግ ላይ ከደቡብ አፍሪካ ጋር የምድብ ሁለተኛ ጨዋታቸውን የሚያደርጉ ይሆናል። ምድቡንም ጋና በሦስት ነጥብ መምራት ጀምራለች።