ኢትዮጵያ ቡና እና ሀበሻ ቢራ ውላቸውን አድሰዋል

ከ2004 ጀምሮ የዘለቀው የቡና እና የሀበሻ ጥምረት ለቀጣይ አምስት ዓመታት እንደሚቀጥል ታውቋል።

ዛሬ ረፋድ በቤስት ዌስተርን ሆቴል በተፈረመው የስፖንሰርሺፕ ውል የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ገዛኸኝ ወልዴ እንዲሁም የሀበሻ ቢራ አ.ማ የማርኬቲንግ እና የሽያጭ ክፍል ኃላፊዎች የሆኑት ወይዘሮ አፍል አምበርብር እና አቶ ክንፈሚካኤል ፀጋዬ ተገኝተዋል። ባለ ስምንት አንቀፅ የሆነው ውልም ሀበሻ ቢራ ምርቶቹን ለቀጣዮቹ አምስት ዓመታት በኢትዮጵያ ቡና በኩል ለማስተዋወቅ በተለያዩ መልኮች የሚከፍላቸውን ክፍያዎች ያስቀምጣል። በዋነኝነት ሀበሻ በመጀመሪያዎቹ ሁለት የውል ዓመታት በዓመት የ18 ሚሊየን ብር ክፍያ ሲፈፅም በቀሪዎቹ ሦስት ዓመታት በሚኖረው የገበያ እና የኢኮኖሚ ሁኔታ ላይ ተመስርቶ በየዓመቱ ከ5℅ ያላነሰ ጭማሪ እንደሚያደርግ ተጠቁሟል።

ከዋናው ዓመታዊ ክፍያ በተጨማሪነት ለሁሉም የፆታ እና የዕድሜ ዕርከን ቡድኖች ለሚሆን ትጥቅ እና ሪፐሊካ ማሊያ 4.5 ሚሊዮን ፣ ለኢትዮጵያ ቡና ዓመታዊ ቤተሰብ ሩጫ 3.75 ሚሊየን ፣ ሁለቱ አካላት በጋራ ለሚያዘጋጇቸው አራት ሌሎች ዝግጅቶች 2 ሚሊየን ፣ ዋናው ቡድን የሊግ ቻምፒዮን ከሆነ 2.7 ሚሊየን ሁለተኛ ከወጣ ደግሞ 900 ሺህ ፣ ዋናው ቡድን በሊጉ በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ለተጫዋቾች ማበረታቻ በየጨዋታው ከ6000-8000 እንዲሁም ለክለቡ ተጫዋቾች ማጓጓዣ የሚሆን አውቶብስ ግዢ የ 12.5 ሚሊየን ብር ክፍያዎች ከሀበሻ ቢራ አ.ማ ይጠበቃል።

በሀበሻ ቢራ ተወካዮች በኩል እንደተነገረው ድርጅቱ ባሳለፍነው ዓመት ውድድር ላይ ከስምምነቱ ያገኘውን ተጨባጭ ጥቅም በጥናት ባያረጋግጥም በተለይም የማልት ምርቶቹን ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በመስራቱ የማስተዋወቅ ዕድሉ እንደሰፋ ዕምነታቸውን ገልፀዋል። በዚህም በሀገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ፣ በኮቪድ 19 ወረርሺኝ እና ሌሎች ውጪያዊ ጉዳዮች ምክንያት የሽያጭ መጠን ቀንሶባቸው አንዳንድ ፕሮጀክቶችን ለማቆም ቢገደዱም ከኢትዮጵያ ቡና ጋር መስራት ለመቀጠል ግን መወሰናቸውን ከጋዜጠኞች በኩል ከቀረቡላቸው ጥያቄዎች በመነሳት አብራርተዋል።

አቶ ገዛኸኝ ወልዴ በበኩላቸው አክሲዮን ማህበሩ ለክለቦች ማልያዎችን ለማሰራት ምርጫ ቢያቀርብም ክለባቸው የስፖንሰሮቹን ፍላጎት ባሟላ መልኩ በራሱ ለማሰራት መወሰኑን አንስተዋል። ከዚህ ውጪ ክለባቸው የፋይናንስ አቅሙን ለማጎልበት ሌሎች ተጨማሪ ስፖንሰርሺፕ ንግግሮችን ያደረገ እንደሆነ ጠቁመው አምና በኮቪድ ሳቢያ ያልተካሄደው የኢትዮጵያ ቡና ቤተሰብ ሩጫ ውድድር ጥቅምት መጨረሻ ላይ እንዲደረግ እንቅስቃሴ መጀመራቸውን አንስተዋል።

ያጋሩ