የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ውድድር ዛሬ በተካሄዱ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎች አዳማ እና አርባምንጭ ለፍፃሜ ዋንጫ ማለፋቸውን አረጋገጠዋል።
በመጀመርያ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና ከአርባምንጭ ከተማ ያገናኘው ጨዋታ በመለያ ምት አርባምንጭ አሸናፊ ሆኗል።
በአሰልጣኝ ደግፌ የሚመሩት ቡናዎች በኳስ ቁጥጥሩም ሆነ ጨዋታውን በሚፈልጉት መንገድ በመቆጣጠርም ከአርባምንጭ በተሻለ ሙሉ ዘጠና ደቂቃ ብልጫ ወስደው መጫወት ችለው ነበር። ሆኖም በጨዋታው ክፍለ ጊዜ ለጎል የቀረበ ሙከራ ያደረጉት አንዴ ነበር። ወደ ፊት ተስፋ ከሚጣልበት የመስመር አጥቂው ሀምዛ አማካኝነት ከመስመር የተሻገረለትን ኳስ አምስት ከሀምሳ ውስጥ ኳሱን ተቆጣጥሮ ተከላካዮችን አሸማቆ በማለፍ የመታው ኳስ ግብጠባቂውን አልፎ ጎል ገባ ሲባል ተከላካዩ ተደርቦ ያወጣው ቡና በኩል ግልፅ ሙከራ ነበር።
በቀድሞ ተጫዋች አሰልጣኝ አዱኛ ገላነህ የሚመሩት አርባምንጮች እስካሁን ከመጡበት ጥንካሬ ዛሬ ወርደው የራሳቸውን የጨዋታ ዘይቤ ይዞ ከመቅረብ ይልቅ የቡናን የኳስ ቁጥጥር ለማክሸፍ በማሰባቸው ከእንቅስቃሴ በመውጣት በወተሰነ መልኩ በመልሶ ማጥቃት ከሚፈጥሩት አደጋ ውጭ እድሎችን ሲፈጥሩ አልተመለከትንም። ጨዋታውም ጎል ሳይቆጠርበት መደበኛው የጨዋታው ክለፍለ ጊዜ በመጠናቀቁ በተሰጠው የመለያ ምት አርባምንጮች በግብጠባቂያቸው ጥረት ታግዘው 4-2 በማሸነፍ ለፍፃሜው ጨዋታ ማለፋቸውን አረጋግጠዋል።
በዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ሆኖ የቀጠለው ተጠባቂው ጨዋታ ጥሩ ፉክክክር አሳይቶን በስተመጨረሻ አዳማ ከተማ ሀዋሳ ከተማን 4-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። በሩብ ፍፃሜ ጨዋታ የነበረባቸውን ድክመት በሚገባ አስተካክለው የመጡት የአዳማ ከተማው ዋና አሰልጣኝ አፈወርቅ ለዋንጫ ተገማች ቡድን መሆናቸውን በእንቅስቃሴያቸው አስመልክተውናል። ምንም እንኳን አስከ ዕረፍት ብዙም የጎል ዕድሎችን መፍጠር ባይችሉም። በመጀመርያው አጋማሽ የተሻለ እንቅስቃሴ ያስመለከቱን በአሰልጣኝ ጴጥሮስ ኤልያስ የሚመሩት ሀዋሳዎች የአዳመን የመከላከል አደረጃጀት ከፍተው ጎል ማስቆጠር ይቸገሩ እንጂ ጎል ለማስቆጠር ጥረት አድርገው ነበር።
የመጀመርያው አጋማሽ ጎል ያልተስተናገደበት የሁለቱ ጨዋታ በዕረፍት መልስ አራት ጎል ሊቆጠርበት ችሏል።
በጥሩ መንገድ ከቀኝ መስመር የገቡት አዳማዎች ከተሻጋሪ ኳስ ኃየለዓምላክ አሰፋ በግንባር በመግጨት የመጀመርያውን ጎል አስቆጥረዋል። ከጎሉ መቆጠር በኃላ የቡድናቸውን እንቅስቃሴ የሚቀይሩ የተጫዋቾች ለውጥ ሁለቱ ሲልያደረጉ በዚህ ቅያሪ አዳማ ተጠቃሚ ሀዋሳ ተጎጂ ሆኗል። በተለይ ሀዋሳ በዕለቱ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረውን የግራ መስመር ተከላካይ ጌቱ ሕዝቄል ተቀይሮ መውጣቱ ቡድኑን ዋጋ አስከፍሎታል። በአንፃሩ ተቀይረው የገቡት የአዳማ ተጫዋቾች ጎል በማስቆጠር ልዮነት ፈጣሪ ተጫዋች ሆነዋል። በዚህ ሂደት ተቀይሮ የገባው ቃሲም ሲራጅ ቡድኑን እንዲረጋጋ ያደረገች ግሩም ሁለተኛ ጎል አስቆጥሮ አዳማን መሪ ማድረግ ችሏል።
ሀዋሳዎች ጎል ከተቆጠረባቸው በኃላ እየወረዱ በመምጣት ተጨማሪ ጎል ሊቆጠርባቸው ችሏል። ሌላኘው ተቀይሮ የገባው አስተርዮ አሸናፊ የሀዋሳን የመከላከል ክፍተት ተጠቅሞ አፈትልኮ በመግባት ለቡድኑ ሦስተኛ ጎል አስቆጥሯል። ጨዋታው በዚህ ውጤት አበቃ ሲባል የሀዋሳው ግብጠባቂ ያብስራ ለቡድን አጋሩ አቀበልኩ ያለው ኳስ ቃሲም ሲራጅ እግር ስር ደርሳ በቀላሉ ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ አራተኛ ጎል አስቆጥሮ አዳማ ከተማ 4-0 አሸንፈው ለፍፃሜው ጨዋታ ማለፋቸውን አውቀዋል።
ከ17 ዓመት በታች የታዳጊዎች ውድድር በታሪክ የመጀመርያውን ተሳትፎ ያደረገው አርባምንጭ ከተማ በውድድሩ ከፍተኛ ልምድ ካለው አዳማ ከተማ ጋር በቀጣይ ሳምንት ማክሰኞ የፍፃሜ ጨዋታቸውን የሚያደርጉ ሆነዋል።
ከፍፃሜው ጨዋታ አስቀድሞ ኢትዮጵያ ቡና ከሀዋሳ ከተማ ጋር የደረጃ ጨዋታ የሚያደርጉ ይሆኗል። ለውድድሩ ከፍተኛ ትኩረት የሰጠው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ዋናው ፀሐፊው አቶ ባህሩ ጥላሁን የዛሬውን ጨዋታ በቦታው በመገኘት ሲከታተሉ ተመልክተናል።