ዋልያዎቹ አዲስ አበባ ገብተዋል

የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የምድብ የመጀመሪያ ጨዋታውን ለማከናወን ወደ ጋና ያመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ምሽት ላይ አዲስ አበባ ገብቷል።

በአሠልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ኳታር ለምታስተናግደው የዓለም ዋንጫ ለማለፍ በምድብ ሰባት ከጋና፣ ደቡብ አፍሪካ እና ዚምባቡዌ ጋር እንደተደለደለ ይታወቃል። ቡድኑም የምድብ የመጀመሪያ ጨዋታውን ለማድረግ በሳምንቱ መጀመሪያ ወደ ጋና አምርቶ በትናንትናው ዕለት ጨዋታውን አድርጎ ነበር።

በጨዋታው አንድ ለምንም የተረታው ነገርግን ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ያሳየው ብሔራዊ ቡድኑም ዛሬ ምሽት አዲስ አበባ መግባቱ ታውቋል። የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ እና የጽሕፈት ቤት ኃላፊው አቶ ባህሩ ጥላሁንም በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ተገኝተው ለቡድኑ አቀባበል ማድረጋቸው ታውቋል።

35 አባላትን የያዘው ስብስቡም ዛሬ አዳሩን በጁፒተር ሆቴል በማድረግ በነገው ዕለት ሁለተኛ የምድብ ጨዋታውን ወደሚያደርግበት ባህር ዳር ከተማ እንደሚያመራ ታውቋል። ብሔራዊ ቡድኑም የፊታችን ማክሰኞ ከዚምባቡዌ ጋር በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ጨዋታውን የሚያደርግ ይሆናል።

ያጋሩ