የኢትዮጵያ ቀጣይ ተጋጣሚ አዲስ አበባ ደርሷል

የፊታችን ማክሰኞ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ጋር ጨዋታ የሚያደርገው የዚምባቡዌ ብሔራዊ ቡድን ከደቂቃዎች በፊት አዲስ አበባ ገብቷል።

በምድብ ሰባት ከኢትዮጵያ፣ ጋና እና ደቡብ አፍሪካ ጋር የተመደበው የዚምባቡዌ ብሔራዊ ቡድን በትናንትናው ዕለት በሜዳው ከደቡብ አፍሪካ ጋር ተጫውቶ ነጥብ እንደተጋራ ይታወቃል። ብሔራዊ ቡድኑም ሁለተኛ የምድብ የማጣሪያ ጨዋታውን ለማድረግ በዛሬው ዕለት ወደ ሀገራችን በረራ ያደረገ ሲሆን ከደቂቃዎች በፊትም ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ እንደደረሰ ታውቋል።

ብሔራዊ ቡድኑ ምሽት ላይ ሀገራችን ከመድረሱ ከሁለት ቀናት በፊት ሁለት ግለሰቦች ቀድመው መምጣታቸው ተገልጿል። ሁለቱ አካላትም ከትናንት በስትያ አዲስ አበባ ከደረሱ በኋላ ወዲያው ወደ ባህር ዳር በማቅናት ቡድናቸው የሚያርፍበት ሆቴል እና ተያያዥ አስፈላጊ ነገሮች ሲያመቻቹ እንደነበር ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል።

ከሁለቱ ግለሰቦች ውጪ ግን 38 የቡድኑ አባላት በአሁኑ ሰዓት ከቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ እየወጡ ነው። ልዑካን ቡድኑም ዛሬ አዳሩን በአዝማን ሆቴል በማድረግ ነገ ረፋድ 4 ሰዓት ወደ ባህር ዳር የሚያቀና ይሆናል።