ዋልያዎቹ ለመከላከያ ሠራዊት ደም ለግሰዋል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ዛሬ ከሰዓት በውዳሴ ዲያግኖስቲክ ማዕከል በመገኘት ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ደም ለግሰዋል።

ኳታር ለምታስተናግደው የ2022 ዓለም ዋንጫ ለማለፍ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዎችን እያደረገ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በትናንትናው ዕለት የዚምባቡዌ አቻውን በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም አስተናግዶ አንድ ለምንም ማሸነፉ ይታወሳል። የብሔራዊ ቡድኑ አባላት አዳራቸውን እዛው ባህር ዳር ካደረጉ በኋላ ዛሬ ቀጥር ወደ አዲስ አበባ መጥተዋል። ልዑካን ቡድኑ አዲስ አበባ ከደረሰ በኋላም በቀጥታ ወደ ጁፒተር ኢንተርናሽናል ሆቴል በማቅናት ምሳ ተመግቧል።

ከፊታቸው አህጉራዊ ጨዋታዎች ካለባቸው ፋሲል ከነማ እና ኢትዮጵያ ቡና የመጡ ተጫዋቾች ውጪ ቡድኑ ውስጥ የሚገኙት ተጫዋቾች ወደየቤታቸው ሳይበተኑ በጎ አላማ ለማከናወን 8 ሰዓት ሲል ቦሌ አካባቢ ወደሚገኘው ውዳሴ ዲያግኖስቲክ አምርተዋል። በህክምና ማዕከሉም ከተጠቀሱት ተጫዋቾች ውጪ ያሉት ተጫዋቾች እና የአሠልጣኝ ቡድን አባላት ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ደም ለግሰዋል።

ተጫዋቾቹ እና አሠልጣኞቹ ደም ከመለገሳቸው በፊት ደግሞ አጠር ያለ ጋዜጣዊ መግለጫ በውዳሴ ዲያግኖሰስቲክ ባለቤት እና ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ዳዊት ኃይሉ፣ በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የሥራ-አስፈፃሚ አባል አቶ አበበ ገላጋይ፣ በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የፅሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁኝ እንዲሁም በብሔራዊ ቡድኑ አሠልጣኝ ውበቱ አባተ እና አምበሉ ጌታነህ ከበደ አማካኝነት ተሰጥቷል። በቅድሚያም የውዳሴ ዲያግኖስቲክ ዋና ሥራ-አስፈፃሚ አቶ ዳዊት ኃይሉ ንግግር አድርገዋል።

“ዛሬ የተገናኘነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ከውዳሴ ዲያግኖስቲክ ጋር በመተባበር የደም ልገሳ እንዲያደርጉ ነው። እንደምታውቁት የጿጉሜ ወር ብዙ ደጋግ ነገሮች የሚደረጉበት ነው። እኛም እንደ ተቋም በዚህ ወር እያደረግናቸው ያሉ ስራዎች አሉ። አሁን ደግሞ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ደም መስጠት እንፈልጋለን ባሉት መሰረት ይህንን ዝግጅት አዘጋጅተናል።” ብለዋል።

የእሳቸውን ንግግር ተከትሎ ደግሞ አቶ አበበ ገላላይ “የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ከዚህ ቀደም የህክምና ጉዳዮችን በተመለከተ ከውዳሴ ጋር ለመስራት ተፈራርሞ ነበር። ትናንት ብሔራዊ ቡድናችን ሀገርን እንዳስደሰተ ይታወቃል። የመከላከያ ሰራዊትም በውጤቱ እንደተደሰተ ይታወቃል። አሁን ደግሞ ለወገናችን ያለንን አጋርነት ለማሳየት ደም ለመለገስ መጥተናል።” በማለት አጠር ያለ ንግግራቸውን አሰምተዋል።

ደም ለመለገስ የመጡ የብሄራዊ ቡድኑ ተጫዋቾች እና አሠልጣኞች፣ የህክምና ማዕከሉ ሰራተኞች እንዲሁም የሚዲያ አካላት በተገኙበት በዚህ መርሐ-ግብር ላይ በቀጣይ ንግግር ያደረጉት አቶ ባህሩ በበኩላቸው እንኳን ደህና መጣችሁ ካሉ በኋላ በትላንቱ ጨዋታ በተገኘው ድል እንኳን ደስ አላችሁ ብለው ቡድኑ ለአዲስ አመት ውጤቱን እንደ ስጦታ ስላበተከተ አመስግነዋል። ዋና ፀኃፊው አክለውም “ከውዳሴ ጋር በአጋርነት መስራት ከጀመርን በኋላ በተለያዩ ስራዎች ላይ እየተሳተፍን እንገኛለን። አሁን ደግሞ ለሰው ልጅ አስፈላጊ የሆነውን ደም ለመለገስ እዚህ ተገኝተናል።” ብለዋል።

መድረኩን የተረከቡት የዋልያው አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ደግሞ “ዋናኛው ግዴታችን ኳስ ተጫውቶ ሀገርን ማስደሰት ነው። ይሄንን ደግሞ ትናንት አሳይተናል።ዛሬ ደግሞ ማኅበራዊ ኃላፊነታችንን ተወጥተን ከሀገር ጎን መሆናችንን ለማሳየት ተገኝተናል። ትናንት ሜዳ ላይ ተጫዋቾቹ ደም ሰጥተዋል። ዛሬ ደግሞ ዋናውን ደም ለመለገስ መጥተዋል። ይህንን ለማድረግ ደስ ብሎን ነው የመጣነው።” ካሉ በኋላ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ መልካም ዐዲስ ዓመት ብለው ሀሳባቸውን ቋጭተዋል። የዋና አሠልጣኙን ንግግር ተከትሎ ጌታነህ ከበደም “ደም በመለገሳችን በጣም ደስታኖች ነኝ።” ሲል ተደምጧል።

እንደተገለፀው ከፋሲል ከነማ እና ኢትዮጵያ ቡና የተጠሩ ተጫዋቾች ውጪ ሌሎቹ ተጫዋቾች ተገቢውን ምርመራ አድርገው ደም ሲለግሱ ቦታው ድረስ አምርተን ተመልክተናል። የቡድኑ አባላት ከደም ልገሳው ጎን ለጎንም ድጋፍ የሚሹ አካላትን እና ህሙማንን ሲጠይቁ እና ሲያበረታቱ ታዝበናል።

የመከላከያ ሰራዊትን ወክለው በቦታው የተገኙት ኮሎኔል አብዲሳ ታደሠ በበኩላቸው ለሰራዊቱ ለተደረገው ተግባር ምስጋና ያስተላለፉበትን ተከታዩን መልዕክት ተናግረዋል።”በመጀመሪያ ዋልያው እኛንም እንደ ተቋም ሀገርንም በጣም ነው ያኮራው። በዚህም በጣም ነው የተደሰትነው። ተጫዋቾቹ ትናንትና ደም ነው ሜዳ ላይ የለገሱት። ዛሬ ደግሞ ሌላ ደም ለመለገስ በመምጣታችሁ በጣም ደስ ብለናል። በቀጣይም ጥሩ ውጤት እንዲገጥማችሁ እንመኛለን። ለተደረገልን ነገር እናመሰግናለን።” ብለዋል።

ያጋሩ