የ55 ዓመቱ የዚምባብዌ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሠልጣኝ ዝድራቭኮ ሎጋሩሲች በነገው ዕለት ቡድናቸውን የኢትዮጵያ አቻውን ከመግጠሙ በፊት ለጋዜጠኞች አስተያየት ሰጥተዋል።
ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋር ለዓለም ዋንጫ ለማለፍ የተደለደለው የዚምባቡዌ ብሔራዊ ቡድን ሁለተኛ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታውን ለማከናወን በትናንትናው ዕለት ባህር ዳር እንደደረሰ ይታወቃል። ብሔራዊ ቡድኑን የሚያሰለጥኑን ክሮሺያዊው የ55 ዓመት አሠልጣኝ ዝድራቭኮ ሎጋሩሲች ቡድናቸውን አመሻሽ ላይ በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ልምምድ ካሰሩ በኋላ ለብዙሃን መገናኛ አባላት መግለጫ ሰጥተዋል። አሠልጣኙም የጋዜጠኞች የቀረቡላቸውን ተከታይ ጥያቄዎች መልሰዋል።
ስለጨዋታው…?
በመጀመሪያ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሁላችንንም ያስገረመ ብሔራዊ ቡድን መሆኑን መግለፅ እወዳለሁ። አጨዋወታችሁ ከጠበቅነው በላይ ነው ፤ ውጤቱም ጋናዊያኑን ምን ያህል እንዳስቸገራችኋቸው የሚያሳይ ነው። ባየናቸው ሌሎች ጨዋታዎችም ኳስን እንዴት መጫወት እንዳለበት የሚያውቅ ብሔራዊ ቡድን መሆኑን ተረድተናል። ከኳስ ጋር ጥሩ ናቸው ፣ በታክቲኩም የተደራጁ ናቸው። ነገ ሳቢ ጨዋታ እንደሚጠብቀንም እገምታለሁ። በእርግጥ እግርኳስ በመሆኑ ማን የተሻለ ዕድል እንዳለው መገመት ይከብዳል። በእርግጥ ኢትዮጵያ በሜዳዋ መጫወቷ የተሻለ ዕድል እንዲሰጣት የሚያደርግ ነው። ነገሮች እንዴት እንደሚሄዱ ግን የምናየው ይሆናል። በምድቡ የተለየ ዕድል የሚሰጠው ቡድን ያለ አይመስለኝም ኢትዮጵያ ከጋና ጋር ጥሩ መጫወት ችላለች ጋናዎችም እዚህ ሲመጡ ቀላል ጨዋታ የሚጠብቃቸው አይመስለኝም። እኛም ጥሩ ውጤት ይዘን ለመመለስ የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን ፤ ለዛም ነው እዚህ የተገኘነው። ሆኖም በእኛ ላይ ብቻ አይወሰንም የኢትዮጵያ አጨዋወት ላይም ይወሰናል። ለተጋጣሚያችን ተገቢውን ክብር መስጠትም ይኖርብናል። እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ ዚምባብዌያን የኳስ ንክኪ የበዛበት ጨዋታ አድናቂዎች ነን። በመሆኑም አዝናኝ ጨዋታ እንደሚሆን ግምቴ ነው።
በጨዋታው ስለሚኖራቸው አቀራረብ…?
ከኢትዮጵያ ጋር መጫወት ከባድ ነው ምክንያያቱም ከኳስ ጋር በጣም በጣም በጣም ጥሩ ናቸው ፤ ጥሩ ሯጮችም ናቸው። በሜዳቸውም እንደመጫወታቸው ጥሩ ውጤት ይዘው ለመውጣት ይገባሉ ፤ በእኔ አስተያየት በጋናው ጨዋታም መሸነፍ አልነበረባቸውም። አቻ ፍትሀዊ ውጤት ነበር። እንደእነሱ ሁሉ እኛም በተመሳሳይ ጥሩ ውጤት ይዘን ለመውጣት ነው የምንጫወተው።
ከደቡብ አፍሪካ ጋር ስላደረጉት ጨዋታ…?
ከደቡብ አፍሪካ ጋር የነበረው ጨዋታ ነገ እንደሚጠብቀን ጨዋታ ሁሉ ከባድ ነበር። የነገው ጨዋታ ውጤትም ወደ ሁለቱም ቡድኖች የሚሄድበት ዕድል ሰፊ ነው። የደቡብ አፍሪካው ጨዋታ ውጤት ፍትሀዊ ነበር ማለት እችላለሁ። በጨዋታው ላይ ካደረግነው እንቅስቃሴ አንፃር ውጤቱ ለሁለታችንም ጥሩ የሚባል ነበር።
በምድቡ ለሚገኙት ቡድኖች ስለሚሰጠው ግምት…?
ሰዎች ጋናን አስቀድመው ቀጥሎ ደቡብ አፍሪካን ቀጥሎ ዚምባቡዌን ቀጥሎ ደግሞ ኢትዮጵያን ቢያስቀምጡም ለእኔ ከፍ ያለ ግምት የሚሰጠው ቡድን አይኖርም። አፍሪካ ውስጥ ያልተጠበቁ ውጤቶችም ስለሚመዘገቡ አላፊው ቡድን በወረቀት ላይ የሚገመተው ብቻ ላይሆን ይችላል። ባልሳሳት ወረቀት ላይ ጋና እና ደቡብ አፍሪካ ከፍ ያለ ግምት ተሰጥቷቸዋል። ነገር ግን ሜዳ ላይ የተሻለው ቡድን ማን እንደሚሆን የሚታይ ይሆናል።
በቡድናቸው ውስጥ ስላሉት ጉዳቶች…?
በብዛት ለብሔራዊ ቡድን ከሚጫወቱ ተጫዋቾች ውስጥ ሰባት ስምንት የሚሆኑ አብረውን የሉም። ይህ ስድስት በእንግሊዝ የሚጫወቱ እንዲሁም ሁለት አሁን ላይ በአውሮፓ ክለብ እየፈለጉ ያሉት ተጫዋቾችን ያካታል። ነገር ግን ይህንን ሰበብ ማድረግ አንፈልግም። ሌሎች በቡድናችን ውስጥ ያሉት ተጫዋቾች ራሳቸውን የሚያሳዩበት ዕድል አግኝተው የብሔራዊ ቡድኑን ማለያ ለቀጣይ ዓመታት የመልበስ ዕድልን ለራሳቸው ይፈጥራሉ።
ስለሚጠብቁት ውጤት…?
ኢትዮጵያ በሜዳዋ እንደመጫወቷ በጥቂቱም ቢሆን የማሸነፍ ዕድሉ ሊሰጣት ይችላል። ያም ቢሆን እኛም ወደ ሜዳ የምንገባው ጥሩ ውጤት ለማስመዝገብ ነው።