የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አስቻለው ታመነ ባለቀ ሰዓት ባስቆጠረው የፍፁም ቅጣት ምት ጎል የዚምባቡዌ አቻውን አሸንፏል።
የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የምድብ ሁለተኛ ጨዋታውን ከዚምባቡዌ አቻው ጋር ያደረገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በጋና አንድ ለምንም ከተረታበት ጨዋታ ሁለት ለውጦችን አድርጎ ወደ ሜዳ ገብቷል። በዚህም አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ግብ ጠባቂው ተክለማርያም ሻንቆን በፋሲል ገብረሚካኤል እና ታፈሰ ሰለሞንን በመስዑድ መሐመድ ለውጠው ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ታውቋል።
የጨዋታውን የሀይል ሚዛን ወደ ራሳቸው አድርገው መጫወት የጀመሩት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ገና በጊዜ መሪ የሚሆኑበትን ጎል ለማግኘት በአቡበከር አማካኝነት የመጀመሪያ ጥቃት ሰንዝረው ነበር። እጅግ ወደ ራሳቸው ግብ ተጠግተው ሲጫወቱ የነበሩት ዚምባቡዌዎች ደግሞ የመልሶ ማጣቃት አጋጣሚዎችን ብቻ የግብ ማስቆጠሪያ አማራጭ አድርገው መጫወት ይዘዋል።
ጨዋታው 21ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ተጋባዦቹ ጥሩ ለግብ የቀረበ ሙከራ አድርገው ነበር። በዚህም ኖውሌጅ ሙሶና እጅግ ፈጣን የማጣቃት ሽግግር በማድረግ ወደ ግብ በመሄድ የሞከረው ኳስ የግብ ዘቡ ፋሲል ገብረሚካኤል በጥሩ ቅልጥፍና አድኖታል። ይህ ሙከራ ከተደረገ ከአራት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ዋልያው ለግብ የቀረበበት ሁነት ፈጥሯል። በዚህም የቡድኑ አማካይ ሽመልስ በቀለ ከግብ ጠባቂው ጋር አንድ ለአንድ ያገናኘውን ኳስ ለመጠቀም ሲጥር ተከላካዮች ተረባርበው አውጥተውታል።
የኳስ ቁጥጥር ብልጫቸውን በጎል ማሳጀብ የፈለጉት የአሠልጣኝ ውበቱ አባተ ተጫዋቾች በ30ኛው ደቂቃ ሌላ ሙከራ አድርገዋል። በተጠቀሰው ደቂቃ የግራ መስመር ተከላካዩ ረመዳን የሱፍ ከሳጥን ውጪ አክርሮ መትቶ የነበረ ቢሆንም የግብ ዘቡ ታልበርት ሹንባ አክሽፎታል። ከሦስት ደቂቃዎች በኋላም በመጀመሪያው አጋማሽ ከኳስ ጋር ብዙ የታየው አማኑኤል ገብረሚካኤል ከቀኝ መስመር ያሻገረው ኳስ ሽመልስ በቀለ ነክቶት እግሩ ላይ የደረሰው ጌታነህ በመቀስ ምት ኳስ እና መረብን ሊያገናኝ ጥሮ ነበር። ነገርግን ኳስ ለጥቂት የግቡን ቋሚ ነክታ ወጥታለች። በቀሪ የአጋማሹ ደቂቃዎችም ተጨማሪ ሙከራ ሳይስተናገድ ተጫዋቾች ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
በሁለተኛው አጋማሽም የዚምባቡዌን መረብ ለማግኘት መታተር የቀጠሉት ዋልያዎቹ ጠጣሩን የተጋጣሚ የተከላካይ ክፍል መስበር ቀላል ሳይሆንላቸው ቀርቷል። በ53ኛው ደቂቃም የአጋማሹን የመጀመሪያ ሙከራ አድርገው መሪ ለመሆን ጥረው ሳይሳካላቸው ቀርቷል። በዚህ ደቂቃም ረመዳን ያሻገረውን ኳስ ተከላካዮች ሲመልሱት ያገኘው አቡበከር ናስር ኳስ እና መረብን ለማገናኘት ጥሮ ግብ ጠባቂው አድኖበታል።
በመከላከል አደረጃጀታቸው ጠንካራ የነበሩት ዚምባቡዌዎች አሁንም የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚን ብቻ መጠበቅ ይዘዋል። በተለይ ቡድኑ በራሱ ሜዳ ግጥግጥ ብሎ በመከላከል የኢትዮጵያ ተጫዋቾችን የኳስ ቅብብል በማቋረጥ በአንድ እና ሁለት የኳስ ንክኪ ዋልያው የግብ ክልል ለመድረስ ሞክሯል። ይህ ቢሆንም ለጥቃቶቹ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የኋላ መስመር ፈጥን እርምጃ እየወሰደ ግብ እንዳይቆጠር አድርነበር።
ጨዋታው 75ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ሦስት ተጫዋቾችን በአንዴ የቀየሩት አሠልጣኝ ውበቱ አባተ የማጣቃት ሀይላቸውን ለማሻሻል ጥረዋል። ይህ ቢሆንም ግን በ87ኛው ደቂቃ የዚምባቡዌ ተከላካይ የፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ኳስ በእጁ ነክቶ ግብ የሚቆጠርበት አጋጣሚ እስኪፈጠር ድረስ ቡድኑ ኳስ እና መረብን ማገናኘት አልቻለም ነበር።
የሲሸልስ ዜግነት ያላቸው የመሐል ዳኛ በርናርድ ካሚሌ ኳስ በእጅ ተነክቷል ብለው የሰጡትን የፍፁም ቅጣት ምት የተቃወሙት የዚምባቡዌ ተጫዋቾች ጨዋታው ለ6 ደቂቃዎች እንዲስተጓጎል አድርገዋል። በተለይ ግብ ጠባቂው ታልበርት ሹንባ ፍፁም ቅጣት ምቱ እንዳይመታ በማድረግ አጋሮቹን ሲያግባባ እና ጨዋታውን ሲያውክ ታይቷል። አልፎም እሱን ጨምሮ አንዳንድ ተጫዋቾች የፍፁም ቅጣት ምት መምቻውን ቦታ በእግራቸው እየቆፈሩ ውሃ ሲያፈሱ ተስተውሏል። የሆነው ሆኖ የዚምባቡዌ የአሠልጣኝ ቡድን አባላት ተጫዋቾቻቸውን አረጋግተው የፍፁም ቅጣት ምቱ እንዲመታ ሆኗል።
ጌታነህ ከበደ እና ሽመልስ በቀለ በሜዳው አለመኖራቸውን ተከትሎ ቡድኑን በአምበልነት እየመራ የነበረው አስቻለው ታመነ የግብ ዘቡን ወደ ተቃራኒ አቅጣጫ ጥሎ የቡድኑን የአሸናፊነት ጎል አስቆጥሯል። ጨዋታውም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አንድ ለምንም አሸናፊነት ተጠናቋል።
ውጤቱን ተከትሎም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በደቡብ አፍሪካ በአንድ ነጥብ ተበልጦ በሦስት ነጥቦች ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ተቀምጧል።