ድንገተኛ የልብ ድካም (SUDDEN CARDIAC ARREST) በእግር ኳስ – ክፍል 2

በእግር ኳስ ውስጥ የሚከሰቱ ጉዳቶች እና ህመሞችን በምንቃኝበት የሶከር ሜዲካል አምዳችን ከዚህ ቀደም የድንገተኛ የልብ ድካም ምንነትን እና ተያይዘው የሚያጋጥሙ የጤንነት እከሎችን መዳሰሳችን የሚታወስ ነው፡፡ በዚህኛው ጽሁፍ ደግሞ የህክምና መፍትሄዎችን የምንመለከት ይሆናል፡፡

አንድ ተጫዋች ለልብ ህመም ችግር ተጋላጭ መሆኑን ለማወቅ የልብ ምርመራ አይነት የሆነውን ECG መጠቀም አስፈላጊ ነው፡፡ ይህን ምርመራ በሚጠቀሙበት ወቅት ባለሙያዎች ከህመም ጋር የተያያዙ እና ከእንቅስቃሴ ጋር የተያያዙ የልብ አሰራር ለውጦችን መለየት ያስችላቸዋል፡፡

ድንገተኛ የልብ ድካምን ለማከም የሚያስፈልጉ ዋና ዋና ነጥቦች የሚከተሉት ናቸው፡፡

– በአፋጣኝ ችግሩን መለየት

– ጊዜያዊ ምላሽ

– በቶሎ ህይወት የማትረፊያ እርዳታን ማስጀመር (Cardiopulmonary Resuscitation)

– በቶሎ የልብ ስራን የሚመልስ ማሽንን መጠቀም (automated external defibrillator)

ማንኛውም ውድድሮችን የሚያካሂድ ትምህርት ቤት ሆነ ክለብ እና ማንኛውም ተቋም ድንገተኛ የልብ ህመም በሚያጋጥምበት ወቅት በቶሎ መልስን መስጠት የሚያስችሉ መሳሪያዎች በቦታው ተዘጋጅተው መቀመጥ አለባቸው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በእራዳታው ወቅት መደረግ ያለባቸው ቅድመ ሁኔታዎች እና የህክምና እርዳታዎች ግልጽ በሆነ መልኩ ተጽፈው በፖስተር መልክ የውድድሩ ቦታ ላይ መለጠፍ ይኖርባቸዋል፡፡
መደረግ ካለባቸው መፍትሄዎች መካከል አንዱ ተጫዋቾች በሚጎዱበት ወቅት እንዴት በቶሎ የልብ ችግርን ማወቅ እንደሚቻል እንደዚሁም እንዴት በአፋጣኝ ወደ ህክምና ማዕከል መውሰድ እንዳለባቸው እና የመሳሰሉትን ዕርዳታዎች የሚሰጡበትን መንገድ ያቀፈ ስልጠና ለባለሙያዎች መሰጠት አለበት፡፡

አንድ ተጫዋች ያለምንም ንክኪ በሜዳ ላይ ከወደቀ በቅድሚያ መጠርጠር ያለበት የልብ ድካም እንዳጋጠመው ነው፡፡ ስለዚህም የህክምና ባለሙያዎች የዳኛውን ፊሽካ ሳይጠብቁ ወደሜዳ በመግባት የህክምና ዕርዳታውን መጀመር መቻል አለባቸው፡፡ ሌላ ሰው ለአራተኛው ዳኛ መንገር አልያም በቀጥታ ለዋናው ዳኛ ሁኔታውን የማስረዳት ሃላፊነት ይኖርበታል ማለት ነው፡፡ ይህ አዲስ አሰራር በ2014 አለም ዋንጫ ጀምሮ ተግባራዊ መሆን ጀምሯል፡፡ ተጫዋቾቹ ከወደቁ በኃላ መልስ አይሰጡም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የተቆራረጥ እና የሚያጣጥር አተነፋፈስ ሲኖራቸው ከዛ በመቀጠል መተንፈስ አለመቻል ይከሰታል፡፡ እንደ ማንቀጥቀጥ ያለ ስሜትም ሊስተዋልባቸው ይችላል፡፡

በሜዳ ላይ የሚደረጉ እርዳታዎችን ተከትሎ ወደ አምቡላንስ ተጫዋቹን መውሰድ እና አቅራቢያ ወዳለ የህክምና ማዕከል መውሰድ ያስፈልጋል፡፡ በዚህን ወቀት Chest Compression ከ10 ሰከንድ በላይ መቋረጥ የለበትም፡፡ ትክክለኛውን እና ጊዜያዊ እርዳታ ያገኙ ተጫዋቾች እስከ 89 ፐርሰንት ድረስ ከሞት የመትረፍ ዕድል አላቸው፡፡ የተጫዋቾችን ሙቀት መቀነስ እንደ ነርቭ ህመም ካሉ ተጓዳኝ ችግሮች እንደሚከላከል ተረጋግጧል፡፡

በአጠቃላይ ከልብ ህመም ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ አደጋዎች በቂ ዝግጅት ካለማድረግ እና የሰለጠኑ ባለሙያዎችን ካለመያዝ የሚመነጭ ነው፡፡ ስለዚህ ከዚህ ጋር በተያያዘ በሁሉም እርከን የሚገኙ ክለቦች ለእንደዚህ ላሉ ችግሮች ብቁ ሆነው መዘጋጀት ይኖርባቸዋል፡፡

በሀገራችን ከልብ ህመም ጋር ተያይዞ ከበድ ያሉ ጉዳቶች ብሎም ሞት እንዳያጋጥም ፌደሬሽን ፤ ክለቦችና እያንዳንዱ የሚመለከተው አካል በህብረት እና በትኩረት መስራት ይኖርባቸዋል፡፡ ውድድር በሚደረግባቸው ቦታዎች የልብ እርዳታ የሚሰጥባቸው ማሽኖች እና ስልጠና የወሰዱ ብቁ ባለሙያዎች ሊኖሩ ያስፈልጋሉ፡፡