በመጨረሻ ደቂቃ የማሸነፊያ ግብ ያስቆጠረው አስቻለው ታመነ ስለተጋጣሚው ግብ ጠባቂ አነጋጋሪ ድርጊት እና ስለ ጎሏ ሀሳቡን ሰጥቷል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የዚምባብዌ አቻውን 1-0 በረታመት የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የምድቡ ሁለተኛ ጨዋታ የመሀል ተከላካዩ አስቻለው ታመነ በመጨረሻ ደቂቃ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት በማስቆጠር ወሳኝ ሚና ተወጥቷል። ከግቡ ባለፈ የተጋጣሚው ግብ ጠባቂ ታልበርት ሹንባ ፍፁም ቅጣት ምቱ ከመመታቱ አስቀድሞ ጨዋታው እንዲስተጓጎል እና የፍፁም ቅጣት ምት የሚመታበት ቦታ ለአመታት ምቹ እንዳይሆን ሲያደርግ መታየቱ አነጋጋሪ ሆኖ ነበር። ያም ቢሆን አስቻለው በሁኔታው ትኩረቱ ሳይረበሽ ኳስ እና መረብን ማገናኘት ችሏል። ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ስለሁኔታው የተጠየቀው ግብ አስቆጣሪው ተከታዩን ምላሽ ሰጥቷል።
“በቅድሚያ መላውን የኢትዮጵያን ህዝብ እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እፈልጋለሁ። ይህ የአዲስ ዓመት ስጦታ ነው። ለረጅም ደቂቃ ጨዋታውን አቋርጠውት ነበር። ግብ ጠባቂውም የተለያየ ነገር ሲያደርግ ነበር ፤ ከባዕድ አምልኮ ጋር በተያያዘ። ሆኖም ፍፁም ቅጣት ምት በራስ የመተማመን ጉዳይ ነው። እኔም ያንን ብዙ ትኩረት አልሰጠሁትም። ከዚህ በፊት ፍፁም ቅጣት ምት ላይ ብዙ ችግር የለብኝም ፤ የእሱ ተግባርም ላይ ትኩረት አላደረኩኝም። በክለብም በብሔራዊ ቡድንም እመታ ስለነበር እና በእንደዚህ ዓይነት ነገር ስለማላምንበት የግብ ጠባቂው ተግባር አላደናገረኝም ፤ ምንም ውስጤን አልረበሸውም። በጥሩ ሁኔታም ላስቆጥር ችያለሁ።