የዚምባቡዌ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሠልጣኝ ዝድራቭኮ ሎጋሩሲች ሦስት ነጥብ ካስረከቡበት ጨዋታ በኋላ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ጨዋታው እንዴት ነበር?
በቅድሚያ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን እንኳን ደስ አላችሁ ለማለት እፈልጋለሁ ፤ ጨዋታው ተመጣጣኝ ነበር በሁለቱም አቅጣጫዎች እንቅስቃሴዎች ነበሩ። ኢትዮጵያ በመጠኑም ቢሆን ማሸነፍ የሚገባቸው ቢመስልም አቻ ግን ፍትሃዊ ውጤት ይሆን ነበር። ምክንያቱም ሁለታችንም ከዚህ ጨዋታ የሆነ ነገር ለማግኘት የተቻለንን ስለጣርን።
በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃዎች ስለተፈጠረው ግርግር..?
በቅድሚያ በጣም አዝኛለሁ ፤ ዳኛው በጥሩ ሁኔታ ጨዋታውን እየመራ ነበር። ነገርግን በዚያ ደቂቃ ላይ ፍፁም ቅጣት ምት ለመስጠት 100% እርግጠኛ መሆን ይጠይቃል። ነገርግን አስር ሰከንድ ቆይተህ ነው አይደለም የሚል መወላወል ውስጥ ከገባህ ግን በጣም የሚያስቅ ነው። ለዚህም ነው ያ ሁሉ ግርግር የተፈጠረው ፤ ፍፁም ቅጣት ምት ነው ብለህ ካመንክ መስጠት አለበለዚያ ቆይተህ መስጠት የለብህም። ሁለተኛው ተጫዋቾቻችን ቅሬታ እያቀረቡ የነበሩት በቅርበት ተጫዋቹ ከሳጥን ውጭ ወድቋል ብለው ነው እኛ ምስሉን ስላላየን እንደዚህ ነው ማለት አንችልም። በዚህ ደረጃ ባለ ውድድር ላይ ግን መሰል የዳኝነት ስህተቶች መመልከት ግን ከባድ ነው። ሌላው ዳኛው አምስት ተጨማሪ ደቂቃ ነበር። ያሳየው ነገርግን በእኔ የተጫወትነው 20 ሰከንድ ነበር። የሚያስቀው ነገር ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ይህ ለምን ሆነ ብዬ ዳኛውን ስጠይቅ ‘ተጫዋቾችህ መጫወት አልፈለጉም’ የሚል ምላሽ ሰጥቶኝ ሄደ። ካፍ ጉዳዩን ተመልክቶ ውሳኔ ይሰጣል ብለን እንጠብቃለን። ለመሸነፋችን ዳኛውን ተጠያቂ ማድረግ ባንፈልግም እንደ እሱ አይነት የሚያደርጉትን የማያውቁ ዳኞች ግን መታረም ይኖርባቸዋል።