“ይህ ህዝብ ከዚህም በላይ ሌላ ስጦታ ያስፈልገዋል” አሰልጣኝ ውበቱ አባተ

በባህር ዳር ዓለምአቀፍ ስታዲየም ኢትዮጵያ ዚምባብዌን 1-0 ከረታችበት የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የምድብ ጨዋታ በኋላ የዋሊያዎቹ አሰልጣኝ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ስለጨዋታው

በመጀመሪያ መላውን የኢትዮጵያ ህዝብ እንኳን ደስ ያለን ማለት እፈልጋለሁ። ጨዋታው አስቸጋሪ እና ከባድ ጨዋታ እንደሚሆን እርግጠኛ ነበርን። ምክንያቱም ለእኛ የሰጡን ግምት ከፍ ያለ በመሆኑ ወደ ጎላቸው አፈግፍገው በመጫወት በመልሶ ማጥቃት ላይ የተመሰረተ ጨዋታ ሊጫወቱ እንደሚችሉ ገምተን ነበር። ያንን አስከፍተን ለመግባት የሚቻለንን ጥረት አድርገናል ፤ ከዕረፍት በፊትም ከዕረፍት በኋላም። ምንም እንኳን በመጨረሻው የሜዳ ክፍል ላይ ከደረስን በኋላ ጉጉት እና መቻኮል ቢኖርም በሁለቱም አጋማሾች ብልጫ ነበረን። ከሁሉም በላይ የሚያስደስተው ግን ውጤቱን ይዘን መውጣታችን ነው። ትናንት ደቡብ አፍሪካ ጋናን ማሸነፏን ተከትሎ የነጥብ ልዩነቱ የሚቀራረብበት እና ወደ ፉክክር የምንመለስበት ወሳኝ ጨዋታ ስለነበር ሦስት ነጥቡን በማሳካታችን በጣም ደስ ብሎናል። ተጫዋቾቹ ሜዳ ላይ ላሳዩት መነሳሳት እና ቆራጥነት እጅግ በጣም ማመስገን እፈልጋለሁ።

የሽመልስ መጎዳት በጨዋታው ላይ ስለነበረው ተፅዕኖ

ሽመልስ የቡድናችን ጥሩ ተጫዋች ነው። ነገር ግን ከሽመልስ መውጣት ጋር ብቻ ተያይዞ ቡድናችን ላይ ተፅዕኖ ነበር ብዬ መናገር አልችልም። ከዛ ይልቅ ሰዓት በሄደ ቁጥር ጉጉት ነበር። እንዲህ ዓይነት ጨዋታዎች ላይ መገኘት በራሱ ሌላ የመንፈስ ጥንካሬ የሚጠይቅ በመሆኑ ያ ይመስለኛል። የኛ ተጫዋቾች ውጤት ማግኘት ይፈልጋሉ ፤ እነዛ ደግሞ እየተከላከሉ ነው ፤ ሰዓቱ በገፋ ቁጥር የሚፈጠርባቸው ጫና ነበር። ይሄ በራሱ ቡድናችን አንድ ደረጃ ከፍ ማለቱን የሚያሳይ ነው። ቡድኖች በቀላሉ እናሸንፈዋልን ብለው የሚመጡበት ዓይነት ቡድን እንዳልሆነ የሚያሳየን ነው። ያንን ፈተና ማለፍ ላይ ግን አሁንም ቢሆን የአዕምሮ ሥራዎች መስራት እንዳለብን ይሰማኛል።

ግቡ በመጨረሻ ደቂቃ መቆጠሩ ስለፈጠረው ስሜት

እግርኳስ 90 ደቂቃ እና ተጨማሪ ደቂቃ ነው። ጎል ዳኛው ፊሽካ ከነፋበት ሰዓት ጀምሮ መጨረሻ ላይ አልቋል እስከሚልበት በየትኛውም ጊዜ ሊቆጠር ይችላል። ጎሉ የገባበት ደቂቃ የዘገየ መሆኑ በእርግጥ ጫና ውስጥ እንደነበርን የሚያሳይ ነው። በቶሎ ጎል ብናገኝ ጥሩ ነበር። ያ ቢሆን የእነሱን ነቅሎ መውጣት ተከትሎ ብዙ ክፍተቶችን እናገኝ ነበር። በትክክልም ይህ ህዝብ ከዚህም በላይ ሌላ ስጦታ ያስፈልገዋል። በብዙ ጭንቀት ውስጥ ያለ ህዝብ ነው እና አዲስ ዓመትም ነውና አዲስ ነገር የምንጀምርበት በመሆኑ በድል መጀመራችን ለእኛ ትልቅ ነገር ነው። ከጨዋታው በፊት ለህዝቡ የገባነው ቃል በመፈፀሙ ደስ ብሎናል። ሁሉንም እንኳን ደስ ያላችሁ ለማለት እወዳለሁ።

ቡድኑ በትዕግስት እስከመጨረሻው ስለመዝለቁ

ከዕረፍት በኋላ እንሻል ነበር ብዬ ነው የማስበው። በመጀመሪያው አጋማሽ ብዙ ጥድፊያ ነበረብን። በተለይ የመጨረሻው የሜዳ ክፍል ላይ ስንደርስ በጣም እንቸኩል ነበር። በቀላሉ ኳሶችን እንለቅ ነበር። ባላስፈላጊ ሁኔታ ለእነሱ በሚመች መንገድ የተወሰኑ ኳሶችን በረጅሙ መትተን ለእነሱ ሲሳይ ያደረግንበት አጋጣሚ ነበር። በኋላ ግን ወደ ጨዋታው ተመልሰን በትዕግስት ተጫወተናል ከዚያም የታረፉ ኳሶችን በተለይም ከረመዳን በኩል ከተነሱ ሁለት ሦስት ኳሶች ዕድል መፍጠር ችለናል። እና እስከመጨረሻው ለእንቅስቃሴያችን ታማኝ ሆነን መጫወት ፍሬ እንደሚያፈራ ነው ያየንበት ፤ ይህንንም እንቀጥልበታለን። ምክንያቱም አሁንም ቡድኑ መልካም ነገር ላይ እንዳለ ነው የሚሰማኝ። የሚታየውም ያ ነው። በጋናው ጨዋታ የነበሩ ጥያቄዎች ነበሩ። ‘ቡድኑ ወደ ፊት አይሄድም ፣ ሰው ሜዳ ላይ አይገባም ፣ ብዙ አይሞክርም ‘ የሚሉ። የዘነጋነው ነገር ግን የምንጫወተው ጋና ላይ ከጋና ጋር መሆኑን ነው። ከዛም ውጪ ከዚህ በፊት በነበረው ሁኔታ ጎሎችን ከመቀነስ ያለፈ ዓላማ አልነበረንም። በአንድ ጊዜ ከህፃንነት ወደ ጉርምስና ውስጥ አይገባም። ቡድኑ በሂደት በየጊዜው እየጨመረ ያለ መሆኑን ነው ዛሬም ያየነው። ከኒጀር ጨዋታ ጀምሮ የተጋጣሚ አሰልጣኞች የሚናገሩትን የባለሙያዎች አስተያየት ዞር ብለን ብናይ ከምን ወደ ምን እንደመጣን ያሳየናል። ይሄ በራስ መተማመናችንን ይጨምረዋል። ከዚህ በኋላ ኢትዮጵያን ሲገጥሙ ከዚህ ቀደም ይገጥመናል ብለው የሚያስቡትን እንዳያስቡ እያደርግን ነው። በመሆኑም ፈተናው የሚጀምረው አሁን ነው ብዬ ነው የማስበው። በክፍተቶቻችን ላይ ብዙ መስራት የጠበቅብናል ብዬ ነው የማስበው ። ዛሬ ያሳካነው ድል ግን ከምንም በላይ ቀጣዩንም ነገር የምናሳምርበት በመሆኑ ለተከፈለው ነገር ሁሉ ማመስገን እፈልጋለሁ። በጣም ደስተኛ ነኝ። እስከመጨረሻው በትዕግስት በመቆየታቸውም ፍሬ አፍርተናል ብዬ ነው የማስበው።

ያጋሩ