የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሠልጣኝ ብርሃኑ ግዛው ስለ ነገው ወሳኝ የፍፃሜ ጨዋታ ይናገራሉ

👉 “ቡድኔን ኢትዮጵያ ላይ ከማውቀው በላይ እዚህ ጠንክሮ አግኝቼዋለሁ”

👉 “120 ሲባል ድሮ እሁድ እሁድ የሚታየውን የመዝናኛ ዝግጅት ብቻ ነበር የማውቀው (ሳቅ)”

👉 “ውድድሩን በድል እንደምናጠናቅቅ ባለ ሙሉ ተስፋ ነኝ”

👉 “የዋንጫ ተገማች መሆናችን ምንም አያዘናጋንም”

በግብፅ አስተናጋጅነት ለሚከናወነው የአፍሪካ ሴቶች የቻምፒየንስ ሊግ ውድድር ለማለፍ የሴካፋ ዞን የማጣሪያ ውድድር በኬንያ እየተደረገ እንደሆነ ይታወቃል። በዚህ ውድድር ላይ የሚሳተፈው የሀገራችን ተወካይ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክም ምድቡን በበላይነት በማሸነፍ በሳምንቱ መጀመሪያ የዩጋንዳውን ሌዲ ዶቭስ ረቶ ለፍፃሜ ማለፉ ይታወሳል። ቡድኑም በነገው ዕለት ወደ ግብፅ የሚወስደውን ትኬት የሚቆርጥበትን ሦስት ነጥብ ለማግኘት ከውድድሩ አስተናጋጅ ሀገር (ኬንያ) ክለብ ቪሂጋ ኩዊንስ ጋር የፍፃሜ ጨዋታ ያከናውናል። ክለቡን ለፍፃሜ ያደረሱት አሠልጣኝ ብርሃኑ ግዛውንም ሶከር ኢትዮጵያ አግኝታ ተከታዩን አጭር ቆይታ አድርጋለች።

ውድድሩን እንዴት አየኸው?

“በውድድሩ ከምንጠብቀው በላይ ከፍ ብለው የቀረቡ ክለቦች አሉ። ሁለተኛ ደግሞ ገና የሴቶች እግርኳስን እየጀመሩ ያሉ ክለቦች አሉ። ከፍ ያለ ደረጃ ላይ ያሉት ክለቦች ውድድሩ የዘገየባቸው እንደሆነ አስባለሁ። ዝቅ ያሉት እና ብዙ ጎሎች የሚገባባቸው ደግሞ ቀስ ብለው ወደ ጥንካሬ እንደሚመጡ አምናለሁ። የእኛ ንግድ ባንክን ጨምሮ የታንዛኒያው ሲምባ፣ የዩጋንዳው ሌዲ ዶቭስ እና የኬንያው ቪሂጋ ኩዊንስ በውድድሩ የታዩ ጠንካራ ቡድኖች ናቸው። ከእነዚህ ጋርም መጫወት በጣም ፈታኝ ነበር። የሆነው ሆኖ ከፊታችን ያሉብንን ጨዋታዎች እያሸነፍን ለፍፃሜ ደርሰናል። በአጠቃላይ ውድድሩ በጣም ጥሩ ነው። እኛም ጥሩ ጊዜ እያሳለፍን ነው። ይህ ውድድር መኖሩም በምስራቅ አፍሪካ ያለውም የሴቶች እግርኳስ ያሳድጋል። ከቀጣይ ዓመት ጀምሮም በዚህ ውድድር ለመሳተፍ የሀገራችንም ክለቦች ስለሚፈልጉ የሊጉ ውድድር እንደሚጠናከር አስባለሁ።”

እስከ አሁን ቡድንህ ከተጫወታቸው አራት ጨዋታዎች ከባድ ፈተና የገጠመው በየቱ ነው? እንዴት?

“ከተጫወትናቸው አራት ጨዋታዎችም ከቪሂጋ ኩዊንስ እና ሌዲ ዶቭስ ጋር ያደረግናቸው ጨዋታዎች ትንሽ ፈተን አድርገውን ነበር። በግማሽ ፍፃሜ ያደረግነው የ120 ደቂቃ ጨዋታ ደግሞ ከበድ ይል ነበር። እኔ በህይወቴ 120 ደቂቃ ተጫውቼ አላውቅም ነበር። 120 ሲባል ድሮ እሁድ እሁድ የሚታየውን የመዝናኛ ዝግጅት ብቻ ነበር የማውቀው (እየሳቀ)። ነገ በፍፃሜው ከምንጋጠመው ቪሂጋ ኩዊንስ ጋርም የተጫወትነው ጨዋታ ከበድ ይላል። በጣም ቁጭ ብድግ የሚያስብል ጨዋታ ነበር። እንደውም ሴቶች በዚህ ደረጃ መጫወት ይችላሉ እንዴ ያስባለም ነበር። ተጋጣሚያችን ረጃጅም ኳሶች ይጫወታሉ፣ የቆመ ኳስ ይሞክራሉ እንዲሁም ይሮጡ ነበር። እኛ ግን ምንም ቢሆን ኳሱን ይዘን ነበር ስንጫወት የነበረው። በዚህም ሁሉም ተጫዋቾች ታግለው ሦስት ነጥቡን አሳክተውት ነበር። ቀድሜ ያልኩት የሌዲ ዶቭሱም ጨዋታ እልህ አስጨራሽ ነበር። ማሸነፍ ትልቅ ቦታ የሚኖረውም እንደዚህ አይነት ጠንካራ ቡድኖችን ስታሸንፍ ነው። በውጤቱም እጅግ በጣም ረክተን ተደስተን ነበር። ሌሎቹ ሁለት ጨዋታዎች ላይ ግን ምንም ሳንጨነቅ ተዝናንተን ነው የወጣነው።”

የቡድንህን ብቃት እንዴት አገኘኸው?

“በጣም የሚገርም ነው። ሀዋሳ ላይ የሊጉን ውድድር ስናደርግ አሸናፊ ቡድን ስለሆንን ሰዎች አይወዱንም ነበር። አይደግፉንም ነበር። እንዳልኩት አሸናፊ ስለሆንንም ይንጫጩብን ነበር። ግን ይህ አለመወደድ ለዚህ ውድድር ጠቀመን። ቡድኔን ኢትዮጵያ ላይ ከማውቀው በላይ እዚህ ጠንክሮ አግኝቼዋለሁ። ስድስት ወር ውድድሩ ተቋርጦ ተጫዋቾቼ በግላቸው እንዲሰሩ እነግራቸው ነበር። እነሱም አላሳፈሩኝም እራሳቸውን እየጠበቁ ነበር። ይህንን ተከትሎ የቡድኔ ብቃት በጣም ጠንክሯል። በነገራችን ላይ እዚህ (ኬንያ) ያሉ ሰዎች በጣም ነው የሚያከብሩን። የሀገሩ ጋዜጠኞችም ስለእኛ ነው የሚያወሩት። እንቅስቃሴያችንንም በተለየ ሁኔታ ነው የሚዘግቡት። እኛ በሀገራችን ካገኘነው ክብር በላይ ኬንያ ላይ ተከብረናል።”

ቡድንህ በውድድሩ ዋንጫ የማንሳት ቅድመ ግምት በማግኘቱ ምን ተሰማህ?

“ከመጀመሪያው ጨዋታ ጀምሮ ቡድናችን ዋንጫ የማንሳት ግምት አግኝቷል። ይህ ደግሞ በጣም ደስ ይላል። ለሀገርም ኩራት ነው። በፊት በፊት እኮ ከሀገራችን ወጥተን ብዙም አናሸንፍም ነበር። በሴቶች እግርኳስ ደቡብ አፍሪካ ላይ አራተኛ የወጣ ቡድን አለ፣ በመሰረት ማኔ አሠልጣኝነትም በሴካፋ ነሃስ ያመጣንበት ጊዜ ነበር። በተጨማሪም አሠልጣኝ አስራት ከ20 ዓመት በታች ቡድኑን ይዞ በሴቶች እግርኳስ ንቅናቄ ያመጣ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ አሠልጣኝ ሰላምም ያመጣችው ውጤት አለ። ከዚህ ውጪ ግን በሀገር ደረጃ የመጣ በጎ ውጤት የለም። አሁን የሀገራችን የሴት ቡድን ለዋንጫ ውድድር ሲያልፍ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። የሆነው ሆኖ የዋንጫ ተገማች መሆናችን ምንም አያዘናጋንም። ስራችንን ነው ይምንሰራው። በአጠቃላይ ያለውን ጫና አሸንፈን ዋንጫ እናነሳለን ብዬ አስባለሁ። እንደ ባለሙያም ቡድኑ ለዋንጫ በመገመቱ እኮራለሁ። እኔ ብቻ ሳልሆን ሀገራችን ኢትዮጵያ፣ የሀገራችን የሴቶች ቡድን አሠልጣኞች እና ንግድ ባንክም ይኮራል።”

ታሪክ እየሰሩ ስለሚገኙት ተጫዋቾችህ የምትለው አለህ?

“እነዚህን ተጫዋቾች ስናከብር እና ቦታ ስንሰጣቸው ሌሎች ልጆችን እናገኛለን። እግርኳስ ሳላቆም ከዚህ ትውልድ ጋር በመስራቴ እጅግ እድለኛ ነኝ። በዚህ አጋጣሚ ላመሰግናቸው እፈልጋለሁ። የሚባሉትን የሚሰሙ ተጫዋቾች ናቸው ያሉኝ።”

ስለ ሎዛ እና መዲና ጥምረት አንድ ነገር በለን?

“ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት ሎዛ አበራ ብቃቷን እያሻሻለች የመጣች የምታስገርም ተጫዋች ናት። ከመዲና ጋርም ያላት ጥምረት የሚገርም እየሆነ ነው። አሠልጣኝ አስራት የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድንን ሲይዝ ሁለቱ ተጫዋቾች በአንድ የእድሜ ቡድን ተጫውተዋል። በጣም ነው የሚዋደዱት በጣምም ነው የሚከባበሩት። ሎዛ በዓለም እግርኳስ ስሟን ስትተክል መዲና አብራኝ ብትጫወት ብላ የተናገረችውን ነገር መቼም አልረሳውም።

“መዲናም በተመሳሳይ ያለፉትን ሦስት እና አራት ዓመታት ጠንካራ ነበረች ግን እንደዚህ ጎልታ አላየናትም ነበር። ተጫዋቿ ወደ መባከን ነበረች። እኛ አሠልጣኞች ግን ተጫዋቾቻችንን እንዴት መያዝ እንዳለብን ማሰብ አለብን። አሁን መዲና አንገቷን ደፍታ ሥራዋን እየሰራች ነው። ወደፊትም የተሻለ ደረጃ እንደምትደርስ አስባለሁ። የሆነው ሆኖ የሎዛ እና መዲና እንዲሁም የሌሎቹ ተጫዋቾች ትብብር ቡድኑ ግብ እንዲያገባ አድርጓል። በአጠቃላይ ሎዛ እና መዲና ከዚህም በላይ እንደሚሰሩ አስባለሁ። የሁለቱ አሠልጣኝ በመሆኔ እና ክለባችንንም ከፍ በማድረጋቸው በጣም ነው የምደሰትባቸው።”

በነገው ጨዋታ ምን እንጠብቅ?

“የነገው ጨዋታ ቆራጥነት፣ ልብ፣ ወኔ እና ማስተዋል ይፈልጋል። እኔ እና ተጫዋቾቼ ያለንን አቅም በእግርኳስ ውስጥ አውጥተን ለማሳየት ተዘጋጅተናል። ዋንጫ አንስተን የመጀመሪያው ክለብ ለመሆን እና በዋናው ውድድር ላይ የምንሳተፍበት ዕድል ለማግኘት ጨዋታው በጣም ያስፈልገናል። ከዚሁ ጎን ለጎን የሴቶች እግርኳስን ለማሳደግ ስለሚጠቅመን በትኩረት ጨዋታውን እንቀርባለን። ስለዚህ ያለንን ሁሉ አውጥተን ተጫዋቾቻችንን ለማዘጋጀት እየጣርን ነው። አሁን ባለው ሁኔታም ተጫዋቾቹ በጥሩ ሥነ-ልቦና ተዘጋጅተዋል። ውድድሩን በድል እንደምናጠናቅቅ ባለ ሙሉ ተስፋ ነኝ።”

ያጋሩ