ዳዊት ፍቃዱ የፕሪምየር ሊጉን ክለብ ተቀላቅሏል

2005 ላይ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን ዋንጫ አንስቶ የሚያውቀው የአጥቂ መስመር ተጫዋች ዳግም ወደ ሊጉ የተመለሰበትን ዝውውር አገባዷል።

በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ከሊጉ መውረዱን አውቆ የነበረው ጅማ አባጅፋር የትግራይ ክልል ክለቦች በሊጉ አለመሳተፋቸውን ተከትሎ ባገኘው ዕድል በሊጉ መቆየቱን ማረጋገጡ ይታወቃል። ክለቡ በቀጣይ ዓመት ተጠናክሮ ለመቅረብም አሠልጣኝ አሸናፊ በቀለን በመቅጠር አዳዲስ ተጫዋቾችን በመቀላቀል ቢሾፍቱ ላይ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን ጀምሯል። ሶከር ኢትዮጵያ አሁን ባገኘው መረጃ ደግሞ ክለቡ የአጥቂ መስመር ተጫዋቹ ዳዊት ፈቃዱን አስፈርሟል።

የቀድሞ አየር ኃይል እና ኢትዮጵያ ቡና ተጫዋች የነበረው ዳዊት 2003 ላይ ወደ ደደቢት ካመራ በኋላ የሊጉን ዋንጫ 2005 ላይ ማንሳቱ አይዘነጋም። ተጫዋቹም ሰባት ዓመታትን ካገለገለበት ሰማያዊው መለያ በኋላ 2010 ላይ ወደ ሀዋሳ 2011 ላይ ደግሞ ወደ ወልዋሎ ዓ/ዩ አምርቶ የእግርኳስ ህይወቱን ቀጥሏል። በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት መጀመርያ ወደ ኢትዮጵያ መድን አምርቶ በከፍተኛ ሊጉ ያሳለፈው ተጫዋቹ አሁን ጅማን በመቀላቀል የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን ከአዲሶቹ አጋሮቹ ጋር እንደጀመረ አረጋግጠናል።