የፋሲል ከነማ የቻምፒየንስ ሊግ ተጋጣሚ ነገ ማለዳ አዲስ አበባ ይገባል

የፊታችን እሁድ ከፋሲል ከነማ ጋር የመጀመሪያ ዙር የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ የሚያደርገው የሱዳኑ ክለብ አል ሂላል ነገ ማለዳ አዲስ አበባ እንደሚገባ ታውቋል።

በካፍ ስር ከሚደረጉ አህጉራዊ የክለብ ውድድሮች መካከል ትልቅ ትኩረት የሚሰጠው የቻምፒየንስ ሊግ ውድድር ላይ ለመሳተፍ ክለቦች በተለያዩ ዙሮች የማጣሪያ ጨዋታዎችን እንደሚያደርጉ ይታወቃል። የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አሸናፊ ክለብ ፋሲል ከነማም በዚህ ውድድር ላይ ለመሳተፍ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎችን ካለንበት ሳምንት የመጨረሻ ቀናት ጀምሮ ማድረግ ይጀምራል።

በመጀመሪያው ዙር የቅድመ ማጣሪያ መርሐ-ግብር ከሱዳኑ አል ሂላል ጋር እሁድ በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የሚጫወተው ፋሲል ዝግጅቱን እያገባደደ እንደሆነ ተጠቁሟል። የክለቡ ተጋጣሚ አል ሂላልም በሀገሩ ያደረገውን ዝግጅት በማገባደድ ነገ ማለዳ 12:30 አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ እንደሚደርስ ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።

47 አባላት ያሉበት የልዑካን ቡድንም ማለዳ አዲስ አበባ ከደረሰ በኋላ የኮቪድ-19 ምርመራ የሚደረግለት ይሆናል። ምርመራ ካለቀ በኋላ ደግሞ 3:30 ሲል ጨዋታውን ወደሚያደርግበት ባህር ዳር ከተማ እንደሚያመራ ተጠቁሟል። ስብስቡም በዩኒሰን ሆቴል ማረፊያውን አድርጎ የእሁዱን ጨዋታ የሚጠባበቅ ይሆናል።

ያጋሩ