የወቅቱ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዋንጫ ባለቤት ፋሲል ከነማ ከሱዳኑ አል ሂላል ጋር ላለበት የአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ የሚያደርገውን ዝግጅት ሶከር ኢትዮጵያ ቃኝታለች።
በአሠልጣኝ ሥዩም ከበደ የሚመራው ፋሲል ከነማ በ2013 የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ 54 ነጥቦችን በመሰብሰብ የሊጉን ዋንጫ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ከፍ አድርጎ ማንሳቱ ይታወቃል። ክለቡ የሊጉን ደረጃ ሠንጠረዥ አናት ይዞ ማጠናቀቁን ተከትሎ ደግሞ በአፍሪከ ቻምፒየንስ ሊግ ውድድር ላይ የመሳተፍ ዕድል አግኝቷል። ይህንን ተከትሎም ክለቡ በአህጉራዊ ውድድሩ እና በቀጣይ ዓመት ላለው የሊግ ፍልሚያ ተጠናክሮ ለመቅረብ በዝውውር ገበያው ላይ ተሳትፎን አድርጓል።
በቅድሚያ የአሠልጣኙን ውል አድሶ ፊቱን ወደ ተጫዋቾች ያዞረው ክለቡም የነባር ተጫዋቾቹን ውል ካራዘመ በኋላ ሦስት ወሳኝ ዝውውሮችን አከናውኗል። በዚህም ዋንጫዎችን አሸንፈው የሚያውቁትን አስቻለው ታመነ፣ አብዱልከሪም መሐመድ እና ኦኪኪ አፎላቢን ወደ ስብስቡ ቀላቅሏል። ዝግጅቱን ከመጀመሩ በፊት ስብስቡን በተጠቀሰው መንገድ ያጠናከረው ክለቡ መስከረም 2 እና 9 ከሱዳኑ አል ሂላል ጋር ለሚያደርገው ጨዋታ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን ለማድረግ ተጫዋቾቹን ባህር ዳር ላይ ሰብስቧል።
ሰኞ ነሐሴ 3 በባህር ዳር አዲስ አምባ ሆቴል የተሰባሰቡት ተጫዋቾቹም በማግስቱ ጠቅላላ የህክምና ምርመራ ካደረጉ በኋላ ከነሐሴ 5 ጀምሮ ዝግጅት ማድረግ እንደጀመሩ ለማወቅ ተችሏል። በሦስት ምዕራፎች በተከፋፈለው የቡድኑ የዝግጅት ጊዜ ላይ በቅድሚያ ለ14 ቀናት የቆየ አጠቃላይ የልምምድ መርሐ-ግብር እንደነበረ ተረድተናል። የመሰባሰቢያ እና የመመርመሪያ ቀናትን ጨምሮ ባሉት 14 ቀናት የቡድኑ ተጫዋቾች አራት ቀናትን በቀን አንድ ጊዜ፣ ስድስት ቀናትን ደግሞ በቀን ሁለት ጊዜ (አንደኛው የጂምናዚየም) ልምምድ ሰርተው 2 ቀን የእረፍት ጊዜ እንደተሰጣቸው ተመላክቷል። በዚህ የመጀመሪያ ምዕራፍ የቡድኑ የዝግጅት ጊዜም የአካል ብቃት ላይ ያተኮሩ ሥራዎች በትኩረት የተሰሩ ሲሆን ቴክኒካዊ እና ታክቲካዊ ጉዳዮች ላይ የነበሩ ልምምዶች ግን በውስንነት ተሰጥተዋል።
ከነሐሴ 17 ጀምሮ መሰጠት የጀመረው የሁለተኛ ምዕራፍ የቡድኑ ልምምድ እንደ መጀመሪያው ምዕራፍ ለ14 ቀናቶች የቆየ ነበር። በእነዚህ የልምምድ ቀናትም 5 ቀናት በቀን አንድ ጊዜ እንዲሁም 3 ቀናት በቀን ሁለት ጊዜ ልምምድ ሲሰጥ የነበረ ሲሆን 4 ቀናትም ለአቋም መፈተሻ ጨዋታዎች ታስበው ነበር። እንደታሰበው አራት የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎች ባይገኙም ከዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን ጋር በታቀደው መንገድ ጨዋታ ተደርጓል። ከዚህ ውጪ ባሉት ሦስት ቀናት ደግሞ ቡድኑ ለሁለት እየተከፈለ የሙሉ ሜዳ ጨዋታ አከናውኗል። በዚህ የልምምድ ምዕራፍም የአካል ብቃት ልምምዶች እየቀነሱ ሄደው ከኳስ ጋር ያሉ ልምምዶች በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመሩ እንደተሰጡ ታውቋል።
ለብሔራዊ ቡድን ግዳጅ ከስብስባቸው ውጪ የሆኑትን 7 ተጫዋቾች አጥተው ልምምድ ሲሰሩ የነበሩት ፋሲል ከነማዎች በዛብህ መለዮ እና ሱራፌል ዳኛቸው ከዋልያው ስብስብ ውጪ መሆናቸውን ተከትሎ ከታሰበው ቀን ቀድመው የሦስተኛው የቡድኑ የዝግጅት ምዕራፍ ሊጀመር ሲል አግኝተዋቸዋል። ከሁለቱ አማካዮች በተጨማሪ በብሔራዊ ቡድን ውስጥ እያለ ጉዳት አስተናግዶ የነበረው ሀብታሙ ተከስተም ከጉዳቱ አገግሞ ባሳለፍነው ሳምንት መደበኛ ልምምዱን ጀምሯል። እነዚህ ዜናዎች መልካም የሆነላቸው አሠልጣኝ ሥዩም ከበደ በመጨረሻወ ምዕራፍ የዝግጅት ጊዜ ጨዋታዎቹ ላይ ያተኮሩ ልምምዶችን በቀን አንድ ጊዜ በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የመለማመጃ ሜዳ ሲሰሩ ነበር።
ሶከር ኢትዮጵያ ከአንድም ሁለት ጊዜ ባህር ዳር ድረስ ተጉዛ የቡድኑን ዝግጅት ለመመልከት በሞከረችበት ወቅትም ተጫዋቾቹ በጥሩ ሁኔታ ልምምዳቸውን እየሰሩ እንደሆነ ለመታዘብ ችላለች። ክለቡ ከዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታውን በሚያደርግበት ወቅት ጉልበቱ ላይ ጉዳት ካጋጠመው ኪሩቤል ኃይሉ ውጪ ያሉት ተጫዋቾችም በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኙ አውቀናል። ከበድ ያለ ጉዳት ያስተናገደው አማካዩ ግን ከሁለቱ የአል ሂላል የደርሶ መልስ ጨዋታዎች ውጪ እንደሆነ ከክለቡ የህክምና ክፍል ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።
በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ሀገራቸውን ሲወክሉ የነበሩት ሽመክት ጉግሳ፣ይሁን እዳሻው ፣ ያሬድ ባየህ እና አስቻለው ታመነ ደግሞ በትናንትናው ዕለት ስብስቡን መቀላቀላቸው ታውቋል። በዚምባቡዌው ጨዋታ ቋሚ ከነበሩት ያሬድ፣ ይሁን እና አስቻለው ውጪ ሽመክት ጉግሳ በትናንትናው ዕለት ከአጋሮቹ ጋር መደበኛ ልምምዱን መስራት ሲጀምር ሁለቱ የመሐል ተከላካዮች ግን አንድ ቀን እረፍት ተሰጥቷቸው ዛሬ ልምምድ ጀምረዋል።
በነገው ዕለት የመጨረሻ ልምምዱን ከእሁዱ ጨዋታ በፊት የሚያደርገው ፋሲል ከነማ ከነገ በስትያ 10 ሰዓት የሱዳኑን አል ሂላል በመግጠም ረጅሙን የአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ የማራቶን ውድድር የሚጀምር ይሆናል።