በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ቅድመ ማጣርያ የዩጋንዳው ዩ አር ኤን የሚገጥመው ኢትዮጵያ ቡና በቢሾፍቱ ከተማ ሲያደርግ የሰነበተውን ዝግጅት ሶከር ኢትዮጵያ እንዲህ ተመልክታዋለች።
በኢትዮጵያ የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ለዋንጫ ሲፎካከሩ የቆዩት ኢትዮጵያ ቡናዎች በመጨረሻም ፋሲል ከነማን በመከተል ሊጉን በሁለተኝነት አጠናቀዋል። ይህንን ተከትሎም ከ2004 የአፍሪካ መድረክ ተሳትፎ በኋላ ዳግም ወደ አህጉራዊ ውድድር ብቅ ያሉት ቡናማዎቹ የዩጋንዳው ዩ አር ኤን በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ቅድመ ማጣርያ እንደሚገጥሙ ይጠበቃል። ለዚህም ውድድር ይረዳቸው ዘንድ መቀመጫቸውን ቢሾፍቱ ከተማ በማድረግ ዝግጅታቸውን ከጀመሩ ስድስት ሳምንታት አስቆጥረዋል።
በአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ የሚመሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች ባሳለፍነው የውድድር ዓመት ከተጠቀሙባቸው ተጫዋቾች መካከል ግብ ጠባቂው ተክለማርያም ሻንቆ፣ ምንተስኖት ከበደ ፣ ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀን ፣ አዲስ ፍሰሀ ፣ አቤል ከበደ እና ሀብታሙ ታደሰ ከቡድኑ ሲለያዩ በምትካቸው ግብ ጠባቂው በረከት አማረ ፣ነስረዲን ኃይሉ ፣ቴዎድሮስ በቀለ ፣ሥዩም ተስፋዬ እና አቤል እንዳለን ወደ ቡድኑ ቀላቅለዋል። ከዚህ በተጨማሪ ክለቡ ከ17 እና ከ20 ዓመት በታች ቡድኑ አስር ተጫዋቾችን ከዋናው ቡድን ጋር ሲያዘጋጅ ከርሟል።
በቢሾፍቱው ኪሎሌ ሆቴል ማረፊያውን ያደረገው የኢትዮጵያ ቡና ስብስብ ወደ ዝግጅት የገባው ሐምሌ 27 ነበር። በወቅቱ ክለቡ የምክትል አሰልጣኝ ዘላለም ፀጋዬን ኮንትራት አለማራዘሙን ተከትሎ በተፈጠረ አለመግባባት ዋና አሰልጣኙ ካሳዬ አራጌ ከቡድኑ ጋር ወደ ቢሾፍት አልተጋዙም ነበር። ያም ቢሆን አሰልጣኙ ከአምስት ቀናት በኋላ ቡድኑን በመቀላቀላቸው የዝግጅት ጊዜው መንፈስ እንዳይደፈርስ የነበረው ስጋት ተቀርፏል። ከዚህ ጊዜ አንስቶም ለሦስት ሳምንታት በቀን ሁለት ጊዜ ከአካል ብቃት ጋር የተያያዙ ጠንከር ያለ ሥራዎችን ሲሰሩ የሰነበቱት ቡናዎች የጨዋታው ቀን እየተቃረበ ሲመጣ ቀለል ወዳሉ ኳስን መሠረት ወዳደረጉ ልምምዶችን ሲሰሩ ቆይተዋል።
የዝግጅታቸው አንዱ አካል የሆነው የአቋም መፈተጫ ጨዋታዎችን በስፋት ለማግኘት ጥረት አድርገው የነበረ ቢሆንም አብዛኛው የሊጉ ቡድኖች ዘግይተው ዝግጅት የጀመሩ መሆናቸው በታሰበው ልክ የአቋም መለኪያ ጨዋታ እንዳያገኙ አድርጓቸዋል። ነገር ግን ከከተማ ተቀናቃኛቸው ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በመጫወት የቀረውን ጊዜ ለሁለት በመከፈል በሙሉ ሜዳ የእርስ በእርስ ጨዋታዎችን በማድረግ አሳልፈዋል።
ከቡድኑ ተጫዋቾች መካከል ለብሔራዊ ቡድን አገልግሎት አቡበከር ናስር ፣አስራት ቱንጆ ፣ታፈሰ ሰለሞን እና አማኑኤል ዮሐንስ ከስብስቡ ጋር በጋራ በመሆን ሙሉ ዝግጅት ያላደረጉ ሲሆን ዊልያም ሰለሞን ከብሔራዊ ቡድን መቀነሱን ተቀትሎ ከቀናት በፊት የአሰልጣኝ ካሳዬን ቡድን ተቀላቅሎ ልምምዱን መስራት ቀጥሏል። ከዚህ በተጨማሪ አዲስ ፈራሚዎቹ አቤል እንዳለ እና ነስረዲን ኃይሉ ረጅም ጊዜ የወሰደ ጉዳት የነበረባቸው መሆኑን ተከትሎ ዘግይተው ልምምድ የጀመሩ ከመሆናቸው በቀር አብዛኛው የቡድኑ አባላት በመልካም ጤንነት ላይ ይገኛሉ።
ከአንድ ወር በላይ የዘለቀው የኢትዮጵያ ቡና የቢሾፍቱ ቆይታ ነገ የሚደመደም ሲሆን ጠዋት የሚኖራቸውን የመጨረሻ ልምምድ ከሰሩ በኃላ ወደ አዲስ አበባ ይገባሉ። ቡድኑ ከነገ በስቲያ ከዩ አር ኤ ጋር የሚያደርገውን የደርሶ መልስ ጨዋታ የመጀመሪያ ግጥሚያ ዩጋንዳ ካምፓላ የሚያደርግ በመሆኑ ነገ አመሻሽ አራት ሰዓት ላይ ወደ ስፍራው እንደሚያመራ ይጠበቃል።