በአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው መሪነት በሀዋሳ ከተማ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን እየሰራ የሚገኘው ሰበታ ከተማ የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ ቀጥሯል፡፡
ለ2014 የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን በሀዋሳ ከተማ እየሰራ የሚገኘው ሰበታ ከተማ አዳዲስ እና ነባር ተጫዋቾቹን በመያዝ አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ከሳምንታት በፊት ኢንስትራክተር ዳንኤል ገብረማሪያምን በረዳት አሰልጣኝነት የቀጠረው ክለቡ አሁን ደግሞ ሦስተኛ ወይንም የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ በማድረግ ኢያሱ ደስታን ምርጫው አድርጓል፡፡
የቀድሞው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ወላይታ ድቻ ግብ ጠባቂ የነበረው ኢያሱ ኳስን ካቆመ በኃላ ተጫውቶ ባሳለፈበት ወላይታ ድቻ የግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝ በመሆን ጅምሩን ያደረገ ሲሆን ከክለቡም ጋር ከተለያየ በኋላም የተጠናቀቀውን የውድድር ዓመት ከሀድያ ሆሳዕና ጋር አሳልፏል፡፡ ከግብ ጠባቂ አሰልጣኝነት ሚናው በተጨማሪም ክለቡ ከተጫዋቾች እና አሰልጣኞች ጋር ውዝግብ በገባበት ወቅት አንድ ጨዋታ ላይ (ከሀዋሳ ከተማ) ቡድኑን የመራ ሲሆን ድህረ ጨዋታ አስተያየት ሲሰጥ መስተዋሉም የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነበር። አሰልጣኝ ኢያሱ ውሉ ከክለቡ ጋር መጠናቀቁን ተከትሎ ማረፊያውን ሰበታ ከተማ አድርጓል፡፡