የከፍተኛ ሊጉ ክለብ አዲስ አሰልጣኝ ሾሟል

በከፍተኛ ሊጉ ምድብ ለ ጠንካራ ተፎካካሪ የሆነው ጋሞ ጨንቻ አዲስ ዋና አሰልጣኝ ቀጥሯል፡፡

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ ጠንካራ ተፎካካሪ በመሆን ያለፉትን ሦስት ዓመታት እየተወዳደረ የሚገኘው ጋሞ ጨንቻ የተጠናቀቀውን የውድድር ዘመን በምድቡ ከተደረጉ 22 ጨዋታዎች 39 ነጥቦችን በመሰብሰብ ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ ማጠናቀቁ ይታወሳል፡፡ በአሰልጣኝ ማቲዮስ ለማ ሲመራ የነበረው ክለቡ ከአሰልጣኙ ጋር ከተለያየ በኋላ በምትኩ አሰልጣኝ ዓለማየሁ ዓባይነህን በአንድ ዓመት ውል በዛሬው ዕለት ሾሟል፡፡

የቀድሞው የአርባምንጭ ጨጨ ተጫዋች እንዲሁም የአርባምንጭ ከተማ እና ሲዳማ ቡና አሰልጣኝ የነበረው ዓለማየሁ ሀምበሪቾ ዱራሜን ካሰለጠ በኋላ የተጠናቀቀውን የውድድር ዓመት ካለክለብ ማሳለፉ የሚታወስ ሲሆን ለቀጣዩ የውድድር ዓመት ግን ጋሞ ጨንቻን እየመራ በከፍተኛ ሊጉ የምናየው ይሆናል፡፡