“በአፍሪካ መድረክ የኢትዮጵያ ቡናን አጨዋወት ማሳየት እንፈልጋለን ” ኃይሌገብረ ትንሳኤ

በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ቅድመ ማጣርያ የዩጋንዳው ዩ አር ኤን ለመግጠም ወደ ስፍራው ካቀኑ የቡድኑ አባል መካከል ኃይሌገብረ ትንሳኤ ስለጨዋታው ይናገራል።

ኢትዮጵያ ቡና በ2003 የሊጉን ዋንጫ በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ባነሱ ማግስት በአፍሪካ መድረክ ኢትዮጵያን በመወከል ተሳታፊ መሆናቸው ይታወሳል። ለአስር ዓመት ከመድረኩ የራቁት ቡናማዎቹ የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግን 2ኛ ሆነው በማጠናቀቃቸው ዳግም አህጉራዊ ውድድር ብቅ በማለት ከዩጋንዳው ዩ አር ኤ ጋር የመጀመርያ ቅድመ ማጣርያ ጨዋታቸውን እሁድ ከሜዳቸው ውጭ ያደርጋሉ። ለዚህም ውድድር ይረዳቸው ዘንድ መቀመጫቸውን ቢሾፍቱ ከተማ በማድረግ ዝግጅታቸውን ሲሰሩ የቆዩት ኢትዮጵያ ቡናዎች አመሻሽ ላይ ወደ ስፍራው ያቀናሉ። ታዲያ ከጨዋታው አስቀድሞ ከቡድኑ የመስመር ተከላካይ ኃይሌገብረ ትንሳኤ ስለ ዝግጅታቸው እና ስለጨዋታው ያለውን አስተያየት በአጭሩ እንዲህ አጋርቶናል።

የቢሾፍቱ ቆይታቹ ምን ይመስላል?

በጣም ጥሩ ዝግጅት ነበር። በቀን ሁለቴም አንዴም ለኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ውድድር የሚያዘጋጀንን ልምምዳችንን በአግባቡ ሠርተናል። እኔም ሆንኩ የቡድን አጋሮቼ አሰልጣኝ ካሳዬ የሚሰጠንን ስልጠናዎች ለፕሪሚየር ሊጉም እንዲሁም እሁድ ላለብን ጨዋታ ስንዘጋጅ ቆይተናል።

ከዚህ ቀደም ከነበረው ልምምድ የተለየ ዝግጅት አድርጋችኃል ?

ጨዋታው ከአፍሪካ ቡድን ጋር የኮፌዴሬሽን ካፕ መሆኑ የተለየ ካላደረገው በቀር ምንም የተለየ ዝግጅት አላደረግንም። ሁሌም የራሳችንን አጨዋወት መሠረት ያደረጉ ልምምዶችን ነው ስንሰራ ነው የቆየነው። አጨዋወታችንንም ምን ላይ መሰረት እንደሚያደርግ የታወቀ ነው። እሱን ሳንለቅ ጥሩ ዝግጅት አድርገናል። ያም ቢሆን በአፍሪካ መድረክ የኢትዮጵያ ቡናን አጨዋወት ማሳየት እንፈልጋለን። ጥሩ ውጤት በማምጣትም እራሳችንን ለተሻለ ነገር ለማብቃት አስበናል። ከዚህ ውጭ ለየት ያለ የሰራነው ነገር የለም።

ኢትዮጵያ ቡና ከረጅም ዓመት በኃላ ያገኘውን የአፍሪካ መድረክ ተሳትፎ ቡድኑ ውስጥ ምን ዓይነት ስሜት ፈጥሯል?

በጣም የተለየ ስሜት ፈጥሯል። እኔም ሆንኩ አብረውኝ የሚጫወቱ ሁሉ ኢትዮጵያ ቡና ወደ አፍሪካ መድረክ እንዲመለስ ብዙ ጥረቶችን አድርገናል። በጣምም ለፍተንም ነበር። አብዛኛዎቻችን ቡና ቤት ያለን ተጫዋቾች እንዲህ ያለ መድረክ አጋጥሞን አያቅም። ኢትዮጵያ ቡና ትልቅ ክለብ ነው። ይህን ታሪካዊ ዕድል በኛ ጊዜ በመምጣቱ ሁላችንም ደስ ብሎናል።

የቡድኑ ተጫዋቾች ለጨዋታው ያላቸው ዝግጁነት እንዴት ይገለፃል?

በሁሉም ተጫዋቾች ዘንድ ከፍተኛ ተነሳሽነት አለ ለጨዋታውም በደንብ ተዘጋጅተናል። ይህ አጋጣሚ በመምጣቱ በጣም ደስ ብሎናል። ይዘነው የመጣነውን የኳስ እንቅስቃሴ በእሁዱ ጨዋታ ቡድናችን ምን እንደሚመስል ማሳየት እንፈልጋለን። ጥሩ ውጤት በማምጣትም እራሳችንን ለተሻለ ነገር ለማብቃት አስበናል። ሁላችንም ጋር ጥሩ መንፈስ አለ።

ስለተጋጣሚያቹ ቡድን ?

ስለታጋጣሚ ቡድናችን መረጃዎች ሊኖሩን ይችላሉ። ግን የኛ እንቅስቃሴ ይታወቃል በዛ መሠረት ነው የራሳችን ዝግጅት ስናደርግ የቆየነው። የምንጫወትበት ሜዳ ሰው ሰራሽ ሜዳ መሆኑን አውቀናል። ይህ ደግሞ ለእኛ አጨዋወት በጣም አመቺ ነው። ሜዳውንም ታሳቢ ያደረገ ዝግጅት ስናደርግ ቆይተናል።

ከጨዋታው ምን እንጠብቅ ?

ከጨዋታው በፊት እንዲህ ነው ብሎ መናገር ባይገባም። ጨዋታውን በደርሶ መልስ ውጤት በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር እናልፋለን። ሁላችንም ጋር ጥሩ ስሜት አለ። የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች በአፍሪካ መድረክ አስደስተን የኢትዮጵያ ቡና ስምን ከፍ ማድረግ እንፈልጋለን።

ያጋሩ