ሪፖርት | ፋሲል ከነማ በሁለት ጎል ከመመራት ተነስቶ አቻ ተለያይቷል

በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ለመጀመርያ ጊዜ የተሳተፈው ፋሲል ከነማ በቅድመ ማጣርያው የመጀመርያ ጨዋታ ባህር ዳር አለማቀፍ ስታዲየም ላይ አል ሂላልን አስተናግዶ ሁለት አቻ ተለያይቷል።

በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ዐፄዎቹ ጨዋታው በመቆጣጠር የጨዋታ ብልጫ ወስደው ለመጫወት ጥረት ሲያደርጉ ተጠቃሽ ሙከራ በማድረግ ረገድም ቀዳሚ ነበሩ። 3ኛው ደቂቃ ላይ ኦኪኪ አፎላቢ ወደ ግብ ኳስ እየነዳ በሚሄድበት ወቅት በተሰራበት ጥፋት የተገኘውን የቅጣት ምት ሱራፌል ዳኛቸው በጥሩ ሁኔታ ወደ ግብ ቢሞክረውም ግብ ጠባቂ መልሶበታል።

የዐፄዎቹ ተጋጣሚ አል ሂላሎች የፋሲል የቅብብል ሂደትን በማቋረጥ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን መፍጠር ችለዋል። በዚህም 10ኛው ደቂቃ ላይ አብዱል ራውፍ ከሳጥን ውጭ አክርሮ የመታው ኳስን ሚካኤል ሳማኪ ሲያድንበት ከአምስት ደቂቃዎች በኋላ በጥፋት የተገኘውን የቅጣት ምት ሙሀመድ ዋታራ ወደግብ እክሮሮ መትቶ ሚኬል ሳማኪ ተፍቶት ሳላህ አደል ብቻውን ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ ያመከነው በአል ሂላል በኩል ግብ መሆን የሚችል አጋጣሚ ነበር።

በአል ሂላል መልሶ ማጥቃት የተጨናነቁት ዐፄዎቹ 21ኛው ደቂቃ ላይ ያሬድ ባየህ ኳስ በእጁ በመንካቱ የፍፁም ቅጣት ምት ተሰጥቶባቸዋል። የተገኘውንም የፍፁም ቅጣት ምት መሐመድ አብዱረህማን ወደ ግብ ቀይሮት ሂላል መምራት ጀምሯል።

ቶሎ ወደ ጨዋታው ለመመለስ የጣሩት ፋሲሎች በ28ኛው እና 32ኛው ደቂቃ ላይ ሱራፌል ከሳጥን ውጭ ባደረጋቸው ሙከራዎች እና አንዱ ግብ ጠባቂው በመለሰው አንዱን ደግሞ የግብ አግዳሚ ገጭቶ በወጣበትን አጋጣሚ ወደ ግብ ደርሰው ነበር። ከስድስት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ በረከት ወደ ሳጥን ይዞት የገባውን ነገርግን ግብ ጠባቂው ያዳነበት ኳስ ጥሩ የሚባል አጋጣሚ ነበር። ከዚህ ሙከራ በተጨማሪም አል ኢላል የጀመሩትን ኳስ እዛው ላይ በዛብህ መለዮ ቀምቶ ያሻገረለትን ኳስ በረከት በድጋሜ ለመጠቀም ጥሮ ነበር።

መሪ የሆኑት አል ሂላሎች ደግሞ ግብ ካስቆጠሩ በኋላ ተቀዛቅዘው በመከላከል ላይ አተኩረው በመጫወት የመጀመሪያውን አጋማሽ አገባደዋል።

ከእረፍት መልስ ዐፄዎቹ በነበሩበት የማጥቃት እንቅስቃሴያቸው ቀጥለው ጫና አድርገው መጫወት የቻሉ ቢሆንም በተደጋጋሚ በመልሶ ማጥቃት አደጋ በመፍጠሩ የተሳካላቸው ግን ሂላሎች ነበሩ። በጨዋታው 49ኛ ደቂቃ ላይ ኦኪኪ አፎላቢ ከሳጥን ውጭ አክርሮ የመታው ኳስ ግብ ጠባቂ ነክቶት ወጥቶ የተገኘውን የማዕዘን ምት በድጋሚ በጭንቅላቱ ገጭቶ ግሩም ሙከራ ካደረገ ከሁለት ደቂቃ በኋላ አል ሂላል ተጫዋቾች በመልሶ ማጥቃት ኳስ ወጧል ብለው የፋሲል ተጫዋቾች በተዘናጉበት ሰዓት አልፈው በመግባት ከሳማኪ ጋር ተገናኝተው ያስር ሙዝሚል የሞከረውን ሳማኪ በግሩም ሁኔታ አድኖበታል። በድጋሜ ከሦስት ደቂቃዎቸደ በኋላ 54ኛው ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት የተገኘውን ኳስ ሙሐመድ አብዱልራህማን በግሩም ሁኔታ ለያስር ከግራ መስመር በኩል ያሻገረለትን ኳስ ያስር ወደግብ በመቀየር 2-0 መምራት ጀምረዋል።

በተመሳሳይ መንገድ ጎል የማስቆጠር ጥረት ያልተለያቸው አል ሂላሎች በድጋሜ በግራ ሳጥን ጠርዝ ሙሐመድ አብዱልረህማን ያገኘውን ኳስ መትቶ ሚካኤል ሳማኪ ባመከነበት ሌላ ኳስ ጥሩ የሚባል አጋጣሚ ፈጥረው ነበር ።

ፋሲሎች በሁለት ጎል መመራት ከጀመሩ በኋላ የተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ የመሐል ክፍሉን በማጠናከር በተደራጀ ሁኔታ ወደ ማጥቃት የተመለሱ ሲሆን 56ኛው ደቂቃ ላይ በዛብህ መለዮ ሳጥን ውስጥ ያገኘውን ኳስ ቀለል አድርጎ ወደግብ የሞከረው ኳስ ለፋሲል የግብ ልዩነቱን ለማጥበብ መልካም አጋጣሚ ነበር። ከአስር ደቂቃ በኋላ (66ኛው ደቂቃ) ግን በረከት ደስታ ተጨራርፎ የደረሰውን ኳስ ወደ ሳጥን ይዞ በመግባት ለዐፄዎቹ ተስፋ የሰጠች ግብ አስቆጥሯል።

በጎሉ ተነቃቅተው ተጭነው መጫወታቸውን የቀጠሉት ዐፄዎቹ ጨዋታቸውን በአል ሂላል የሜዳ ክፍል በማምረግ የማጥቃት አጋጣሚዎችን ፈጥረዋል። በዚህም 77ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን የተገኘውን ኳስ ሰዒድ ሲጨርፈው ኦኪኪ አፎላቢ አግኝቶ በመጀመርያ የፋሲል ጨዋታው ጎል በማስቆጠር ቡድኑን አቻ አድርጓል።

የማታ የማታ ወደ ጨዋታው የተመለሱት ዐፄዎቹ ይበልጥ አጥቅተው ተጨማሪ ግብ ለማግኘት ናትናኤል እና ዓለምብርሃን ያስገቡ ቢሆንም የግብ ሙከራዎችን ወደ ጎል በመለወጥ አሸናፊ ሳይሆኑ ቀርተዋል። በተለይ መደበኛው ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በጭማሪው ሁለተኛ ደቂቃ ላይ ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ በጭንቅላት ገጭቶ የግብ አግዳሚ የመለሰበት ኳስ ለፋሲሎች እጅግ አስቆጪ ዕድል ነበረች።

ግጭት በበዛበት የመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች አል ሂላሎች ወደ ግባቸው አፈግፍገው በመከላከል ላይ የተጠመዱ ሲሆን የአቻ ውጤቱን ማስጠበቁ ተሳክቶላቸው ጨዋታው 2-2 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል። የመልሱ ጨዋታ የዛሬ ሳምንት እሁድ መስከረም 9 ኦምዱርማን ላይ ይደረጋል ።