በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋር የተደለደለችው ጋና ዋና አሠልጣኟን አሰናብታለች።
ኳታር ለምታስተናግደው የ2022 ዓለም ዋንጫ ለማለፍ የአፍሪካ ሀገራት የማጣሪያ ጨዋታዎችን በምድብ ተከፋፍለው እያደረጉ እንደሆነ ይታወቃል። በምድብ ሰባት ከኢትዮጵያ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ዚምባቡዌ ጋር የተደለደለችው ጋናም በሜዳዋ እና ከሜዳዋ ውጪ የምድብ ጨዋታዎቿን ከኢትዮጵያ እና ደቡብ አፍሪካ ጋር አከናውና ማሳካት ከሚጠበቅባት 6 ነጥቦች ሦስቱን ብቻ ማሳካቷ በሀገሬው ሰው ተቃውሞን እያስነሳ ይገኛል።
ከውጤቱ ጎን ለጎን የብሔራዊ ቡድኑ የቀድሞ ብቃት፣ የአጨዋወት ዘይቤ እና አስፈሪነት አሁን የለም የሚሉ ሀሳቦችም እየተነሱ ይገኛሉ። በተለይ ባሳለፍነው ዓርብ እና ማክሰኞ በተደረጉት የኢትዮጵያ እና ደቡብ አፍሪካ ጨዋታዎች ላይ በታየው እንቅስቃሴ ብዙዎች ደስተኛ እንዳልሆኑ እየተነገረ ይገኛል። ይህንን ተከትሎም የጋና እግርኳስ ፌዴሬሽን የሥራ-አስፈፃሚ ኮሚቴ ስብሰባ በማድረግ የ47 ዓመቱን አሠልጣኝ ቻርለስ አኮኖርን የሁለቱን ጨዋታዎች ሪፖርት ከተመለከተ በኋላ ማሰናበቱ ታውቋል።
በምክትል አሠልጣኝነት በኩል ወደ ዋና አሠልጣኝነት ቦታ 2020 ላይ የመጣው አኮኖር በብሔራዊ ቡድኑ ውስጥ ያሉትን ተጫዋቾች ለአንድ ዓላማ ማጫወት እና መልበሻ ክፍሉን መቆጣጠር እንደተሳነው የጋና ብዙሃን መገናኛዎች ሲዘግቡ መቆየታቸው ይታወቃል። ይህንን ተከትሎም ሀገሪቱን ወደ ዓለም ዋንጫ የማለፍ ተስፋ ለማለምለም ለውጥ እንደሚያስፈልግ በማመን ፌዴሬሽኑ አሠልጣኙን ከነምክትሎቹ ከመንበራቸው አንስቷል።