ለካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ቅድመ ማጣሪያ ወደ ዩጋንዳ ያመራው ኢትዮጵያ ቡና በዩ አር ኤ የ2-1 ሽንፈት ገጥሞታል።
ባለሜዳዎቹ ዩ አር ኤዎች ሁለት ግቦችን ያስቆጠሩበት የመጀመሪያው አጋማሽ እንቅስቃሴ በብዛት በቡና ሜዳ ላይ ያጋደለ ነበር። እንደተለመደው የኳስ ቁጥጥር የበላይነቱን ይዘው የጀመሩት ቡናዎች 10ኛው ደቂቃ ላይ ታፈሰ ሰለሞን ከርቀት ካደረገው ሙከራ ውጪ የኳስ ፍሰታቸው ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መዝለቅ ሳይችል ቀርቷል። ይልቁኑም ዩጋንዳዊያኑ 14ኛው ደቂቃ ላይ የቡናን ቅብብሎች በማቋረጥ በአምበላቸው ሻፊክ ካጊሙ አማካይነት ኢላማውን ያልጠበቀ ሙከራ አድርገው ነበር።
አምበሉ ሻፊክ ከሙከራዉ በኋላ በሁለት አጋጣሚዎች ለስቲቨን ሙኩዋላ እና ቪያኒ ሳካጁጎ ከተቀሙ ኳሶች የግብ ዕድሎችን መፍጠር ችሎ ነበር። የኋላ ኋላም የእነዚህ ሁለት ተጫዋቾች ጥምረት ዩ አር ኤን ተከታታይ ግቦችን እንዲያገኝ አድርገውታል። 23ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ መስመር የተሻማውን ኳስ ቪያኒ በግንባሩ አመቻችቶለት ስቲቨን ሙኩዋላም በተመሳሳይ በግንባሩ ገጭቶ አስቆጥሯል። ስቲቨን 36ኛው ደቂቃ ላይ ከግራው የሳጥኑ ክፍል አክርሮ መትቶ ሲያገባም ከቀኝ መስመር የተሻማውን ኳስ ከአስቆጣሪው ጋር አንድ ሁለት በመቀባበል ያመቻቸለት ቪያኒ ነበር።
ከሁለተኛው ግብ በኋላ ቡናዎች በንፅፅር ሻል ባለ ሁኔታ ከሜዳቸው መውጣት ቢጀምሩም ወደ ማለቂያው ላይ ኃይሌ ገብረትንሳይ ከርቀት የመታው እና ወደ ላይ ከተነሳው ኳስ ውጪ ሌላ ዕድል አላገኙም። ይልቁኑም የቅብብል ስህተቶች ቡድኑን ሌላ ግብ እንዲያስተናግድ ምክንያት ሊሆኑ የተቃረቡባቸው አጋጣሚዎች ቢፈጠሩም ጨዋታው በዩጋንዳዊያኑ 2-0 መሪነት ወደ ዕረፍት አምርቷል።
ከዕረፍት መልስ ከቀደመው በተሻለ ጫና ብለው የጀመሩት ቡናዎች 50ኛው ደቂቃ ላይ አቡበከር ከተከላካዮች ጋር ታግሎ ባመቻቸው እና እንዳለ ደባልቄ ከሳጥኑ መግቢያ ላይ ሞክሮ ለጥቂት በወጣበት ኳስ ማጥቃት ጀምረዋል። ከአምስት ደቂቃዎች በኋላ በተመሳሳይ ሁኔታ ሳጥን ውስጥ ከአቡበከር ኳስ የዳረሰው ዊሊያም ሰለሞን ግን የግል ብቃቱን በሚያሳይ መልኩ የዪ አር ኤ ተከላካዮችን አልፎ ግብ ማስቆጠር ችሏል።
በቀጣዮቹ ደቂቃዎችም ቡናዎች የቅብብሎቻቸው ስኬት ከመጀመሪያው አጋማሽ የተሻሻለ ሆኖ በተጋጣሚያቸው ሜዳ አመዝነው በመንቀሳቀስ ጥሩ የማጥቃት ሂደቶችን ሲፈጥሩ ታይተዋል። ያም ሆኖ ቀጣዩ አደገኛ ሙከራ የዩ አር ኤ ሁለተኛ አምበል ፓትሪክ ሙቡዋ 75ኛው ደቂቃ ላይ ከረጅም ርቀት አድርጎት አቤል ማሞ እንደምንም ያዳነው ነበር። የቡናማዎቹ ቅብብሎች ወደ አደገኛ ሙከራ በተለወጡበት 82ኛው ደቅቃ አቡበከር ከታፈሰ ሰለሞን የተቀበለውን ኳስ አድርሶት እንዳለ ለግብ የቀረበ አጋጣሚ ቢያገኝም ሙከራው በሚያስቆጭ ሁኔታ ወደ ውጪ ወጥቷል።
በቀሪዎቹ ደቂቃዎች በቡድኖቹ መካከል ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ ቢታይም ውጤቱን ለመቀየር የቀረቡ ኢላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎች አልታየም። በባለሜዳዎቹ በኩል በተደረገው የመጨረሻው አስደንጋጭ ጥቃት ግን በጭማሪ ደቂቃ ተቀይሮ የገባው ኦጄሪ ከቡና ተጫዋቾች ስህተት ያገኘውን ኳስ ከቀኝ መስመር አሻምቶ ስቲቨን ሐትሪክ የሚሰራበትን ዕድል ቢፈጥርም አጥቂው ኳሷ ላይ ሳይደርስ ቀርቷል። ጨዋታውም በዚህ መልኩ በ ዩ አር ኤ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ሁለቱ ቡድኖች መስከረም 9 በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታድየም የመልስ ጨዋታውቸውን እንደሚያደርጉ ይጠባቃል።