ሳምሶን አሰፋ አዲስ አዳጊው ቡድንን ተቀላቅሏል


ግዙፉ ግብ ጠባቂ ሳምሶን አሰፋ ወደ ፕሪምየር ሊግ የተመለሰውን ቡድን በአንድ ዓመት ውል ተቀላቅሏል፡፡

የከፍተኛ ሊጉ ምድብ ሐ ሻምፒዮን በመሆን ወደ ኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ማደጉን ያረጋገጠው አርባምንጭ ከተማ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን አዳዲስ እና ነባር ተጫዋቾቹን በጥምረት በማቀፍ እየከወነ ይገኛል፡፡ እስካሁን አራት አዳዲስ ተጫዋቾችን ያስፈረመው ክለቡ አሁን ደግሞ ባለ ልምዱ ግብ ጠባቂ ሳምሶን አሰፋን በአንድ ዓመት ውል ማስፈረሙን ሶከር ኢትዮጵያ ከክለቡ ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል፡፡

የቀድሞው የአየር ኃይል፣ ኤሌክትሪክ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ሀረር ቢራ እና ድሬዳዋ ከተማ እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ግብ ጠባቂ የነበረው ሳምሶን በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን በከፍተኛ ሊጉ ምድብ ለ ተሳታፊ የሆነው አዲስ አበባን ከተማን በመቀላቀል ክለቡን ወደ ፕሪምየር ሊጉ በማስገባት እና ጥቂት ግቦችን በማስተናገድ ትልቁን ሚና የተወጣ ሲሆን አሁን ደግሞ ሌላኛውን አዲስ የፕሪምየር ሊግ ተሳታፊ ክለብ ወደ ሆነው አርባምንጭ ከተማ በማምራት ከክለቡ ጋር ልምምዱን ጀምሯል፡፡

ከክለቡ ጋር በተያያዘ ሁለት የውጪ ዜግነት ያላቸውን ተጫዋቾች ለማስፈረም በዝግጅት ላይ እንዳለ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡

ያጋሩ