ከቀናት በፊት በኢትዮጵያ የተረታችው ዚምባቡዌ አሠልጣኟን አሰናብታለች

በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋር የተደለደው የዚምባቡዌ ብሔራዊ ቡድን ክሮሺያዊውን አሠልጣኝ አሰናብተዋል

በኳታር አስተናጋጅነት ለሚካሄደው ቀጣዩ ዓለም ዋንጫ ለማለፍ በምድብ ሰባት ከኢትዮጵያ፣ ጋና እና ደቡብ አፍሪካ ጋር የተደለደለችው ዚምባቡዌ ሁለት የምድብ ጨዋታዎችን አድርጋ አንድ ነጥብ ብቻ ማግኘቷ ይታወቃል። ይህ ያላስደሰተው የሀገሪቱ የእግርኳስ ፌዴሬሽንም የ55 ዓመቱን ክሮዋት አሠልጣኝ ዝድራቭኮ ሎጋሩሲች ከመንበሩ ማንሳቱን ምሽት ላይ ይፋ አድርጓል።

የካቲት 2020 ላይ የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ሆነው የተሾሙት ሎጋሩሲች እስካሁን 14 ጨዋታዎችን ቢያደርጉም ማሸነፍ የቻሉት አንዱን (ቦትስዋናን 1-0) ብቻ ነው። በስምንቱ ተሸንፈው በአምስቱ አቻ በመውጣትም መጥፎ ሪከርድ አስመዝግበዋል። ይህንን ተከትሎ የዚምባቡዌ እግርኳስ ፌዴሬሽን የሥራ-አስፈፃሚ ኮሚቴ ባደረገው ስብሰባ የአሠልጣኙ ኮንትራት እንዲቋረጥ አድርጓል።

አሠልጣኝ ዝድራቭኮ ሎጋሩሲች እንዲሰናበቱ ከመደረጉ በተጨማሪ የቴክኒካል ቡድኑ አባላትም ዕግድ እንደተላለፈባቸው ለማወቅ ተችሏል። ብሔራዊ ፌዴሬሽኑም በቅርቡ አዲስ አልያም ጊዜያዊ አሠልጣኝ እንደሚሾም ተመላክቷል።

ያጋሩ