አርባምንጭ ከተማ ረዳት አሰልጣኝ ሾሟል

አዲሱ የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተሳታፊው ክለብ አርባምንጭ ከተማ ተጨማሪ ረዳት አሰልጣኝ ሲሾም የነባሮቹን ውል አድሷል፡፡

በአርባምንጭ ከተማ የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን ከጀመሩ ሰንበትበት ያሉት አዞዎቹ አዳዲስ እና ነባር ተጫዋቾችን በጥምረት በማቀፍ አጠናክረው ቀጥለዋል፡፡ በዚህም በ2010 የአርባምንጭ ከተማ ረዳት አሰልጣኝ የነበረው ማቲዮስ ለማን በድጋሚ በረዳት አሰልጣኝነት ሾሟል፡፡ በከፍተኛ ሊጉ ጠንካራ ተፎካካሪ በሆነው ጋሞ ጨንቻ ያለፉትን ሦስት ዓመታት በዋና አሰልጣኝነት ያሳለፈው ማቲዮስ በድጋሚ የአሰልጣኝ መሳይ ተፈሪን ጥሪ ተቀብሎ ዳግም በረዳትነት ተሹሟል፡፡

ከአዲስ ሹመቱ በተጨማሪ ክለቡ ነባር ረዳት አሰልጣኝ የሆኑት አበው ታምሩ እና የግብ ጠባቂ አሰልጣኙ ስለሺ ሽፈራውን ውል ለተጨማሪ አንድ ዓመት አራዝሟል፡፡