አዲስ አበባ ከተማ አራት አዳዲስ ተጫዋቾችን አስፈረመ

በዛሬው ዕለት ግብ ጠባቂ አስፈርሞ የነበረው አዲስ አበባ ከተማ ተጨማሪ አራት አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ ቀላቅሏል፡፡

ከከፍተኛ ሊጉ ምድብ ለ አሸናፊ በመሆን ወደ ፕሪምየር ሊጉ ማደግ የቻለው አዲስ አበባ ከተማ የነባር ተጫዋቾችን ውል ካራዘመ በኋላ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን በከፊል ማረፊያውን በወወክማ በማድረግ መጀመሩ ይታወሳል፡፡ ዝግጅት ከጀመሩ ቀናቶች የሞሉት ክለቡ ከደቂቃዎች በፊት የቀድሞው ግብ ጠባቂው ዳንኤል ተሾመን ከአዳማ ከተማ ያስፈረመ ሲሆን አሁን ደግሞ ተጨማሪ አራት አዳዲስ ተጫዋቾችን አስፈርሟል፡፡

ሳሙኤል ተስፋዬ ከፈራሚዎቹ መካከል ነው። ከቅዱስ ጊዮርጊስ ወጣት ቡድን አድጎ ለዋናው ቡድን ከተጫወተ በኋላ ወደ ባህር ዳር በማምራት ሁለት የውድድር ዓመታት ያሳለፈው የግራ መስመር ተከላካዩ የዋና ከተማውን ክለብ በአንድ ዓመት ውል ተቀላቅሏል። 

ሌላኛው የክለቡ ፈራሚ መሆን የቻለው አማካዩ ኤልያስ አህመድ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ለሰበታ ከተማ፣ ባህር ዳር ከተማ፣ ጅማ አባጅፋር እና የተጠናቀቀውን የውድድር ዓመት ግማሽ ዓመትን በወላይታ ድቻ ካሳለፈ በኋላ ወደ አዳማ ከተማ በመዘዋወር ዓመቱን ያጠናቀቀው ኤልያስ በዛሬው ዕለት ፊርማውን ለአሰልጣኝ እስማኤል አቡበከሩ ቡድን አኑሯል፡፡

በዛሬው ዕለት ከጅማ አባጅፋር ጋር ቀሪ የስድስት ወራት ውል እየቀረው ሊለያይ የቻለው አማካዩ ዋለልኝ ገብሬ ማረፊያው አዲስ አበባ ከተማ ሆኗል፡፡ የቀድሞው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፣ ኤሌክትሪክ፣ ወልዋሎ እና ድሬዳዋ ከተማ ተጫዋች የተጠናቀቀውን የውድድር ዓመት ከዚህ ቀደም መጫወት ወደቻለበት ክለብ ጅማ አባጅፋር በዓመቱ አጋማሽ በመቀላቀል መጫወት የቻለ ሲሆን ከጅማ ጋር በመለያየት ለመዲናይቱ ክለብ በይፋ ፈርሟል፡፡

ያሬድ ሀሰን አዲስ አበባን የተቀላቀለ አዲሱ ፈራሚ ሆኗል፡፡የቀድሞው የወልዲያ፣ መቐለ እና ድሬዳዋ ከተማ የግራ መስመር ተከላካይ የተጠናቀቀውን የውድድር ዓመት በሰበታ ከተማ ያሳለፈ ሲሆን ቀሪ የአንድ ዓመት ኮንትራት ከክለቡ ጋር እያለው በስምምነት በመለያየት ማረፊያውን በአንድ ዓመት ውል አዲስ አበባ ከተማ አድርጓል፡፡