የሲዳማ ዋንጫ ውድድር ሊካሄድ ነው

በሲዳማ ክልል እግር ኳስ ፌድሬሽን አስተናጋጅነት የሲዳማ ዋንጫ ውድድር በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተሳታፊ ክለቦች መካከል በሀዋሳ ከተማ ሊደረግ ነው፡፡

ከተቋቋመ አንደኛ ዓመቱን እየተሻገረ የሚገኘው የሲዳማ ክልል እግርኳስ ፌዴሬሽን በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ የውስጥ እና ሀገር አቀፉ የሆኑ ውድድሮችን በማዘጋጀት አመርቂ ሥራዎችን እየፈፀመ የሚገኝ ሲሆን አሁን ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ የሲዳማ ዋንጫ በሚል ስያሜ በያዝነው ወር አጋማሽ ለማዘጋጀት ማቀዱን የፌዴሬሽኑ ም/ፕሬዝዳንት አቶ አንበሴ አበበ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡ ከመስከረም 16 እስከ መስከረም 25 ድረስ በሚደረገው ውድድር ላይ ስምንት በኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ላይ የሚካፈሉ ክለቦችን ተሳታፊ እንደሚያደርግ እና ክለቦቹም ለመሳተፍ በቂ ምላሽ እንደሰጡ ገልፀውልናል።

በሀዋሳ ይደረጋል ተብሎ በሚጠበቀው ውድድር ላይ የክልሉ ክለቦች የሆኑትን ሀዋሳ ከተማ እና ሲዳማ ቡና ጨምሮ በተጋባዥነት ወላይታ ድቻ፣ ሀድያ ሆሳዕና፣ ባህርዳር ከተማ፣ ወልቂጤ ከተማ፣ ሰበታ ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ እንደሚሳተፉ ታውቋል፡፡

ውድድሩ በሁለት ምድብ ተከፍሎ የሚደረግ ሲሆን የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ከመጀመሩ በፊት ክለቦች አቋማቸውን ቀድመው ወደ ውድድር ከመግባታቸው በፊት እንዲፈትሹ የተሰናዳ መሆኑንንም ጭሞር ለማወቅ ችለናል፡፡ በዚህ ውድድር ማጠናቀቂያ ላይ ለአሸናፊው ከሚዘጋጀው የዋንጫ ሽልማት በተጨማሪ ለኮከብ ተጫዋች ፣ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ፣ ምርጥ ግብ ጠባቂ እና አሰልጣኝ ተብለው ለሚመረጡ ሽልማት መዘጋጀቱንም ጭምር አቶ አንበሴ ነግረውናል፡፡

ከዚህ ቀደም የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ፣ የደቡብ ካስትል ዋንጫ እና የትግራይ ክልል ዋንጫ በሚል በሊጉ ተሳታፊ ክለቦች መካከል ሲደረግ የሚታወስ ሲሆን ይህ የሲዳማ ዋንጫ አራተኛው ውድድር ሆኖ ብቅ ብሏል፡፡

ያጋሩ