የካፍ ሴቶች ቻምፒየንስ ሊግ ውድድር ላይ የሚሳተፉ ክለቦች ተለይተዋል

በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚደረገው የአፍሪካ ሴቶች ቻምፒየንስ ሊግ ውድድር ላይ የሚሳተፉ ስምንት የአህጉሩ ክለቦች ታውቀዋል።

የአፍሪካ እግርኳስ የበላይ አካል የሆነው ካፍ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የእንስቶች የቻምፒየንስ ሊግ ውድድርን ለማድረግ ቀጠሮ መያዙ ይታወቃል። የየሀገራቱ የሊግ አሸናፊ ክለቦችም በስድስት ዞን ተከፋፍለው የማጣሪያ ውድድር በያሉበት ቀጠና ሲያደርጉ ነበር። የኢትዮጵያ ተወካይ የሆነ ንግድ ባንክም በሴካፋ ዞን የማጣሪያ ውድድር ተካፍሎ በፍፃሜው ጨዋታ በኬንያው ቪሂጋ ኩዊንስ ተሸንፎ ወደ ግብፅ የሚወስደውን ትኬት ሳይቆርጥ ቀርቶ ነበር።

ባንክን በፍፃሜው ያሸነፈው የሴካፋ ዞን ተወካይ ቪሂጋ ኩዊንስን ጨምሮ በዋፉ ኤ ዞን የሚገኘው እና በ2017 እንዲሁም 2021 የማሊን ከፍተኛ የሴቶች የሊግ እርከን ያሸነፈው ኤ ኤስ ማንዴ፣ በዋፉ ቢ የነበረውን የማጣሪያ ጨዋታ ያሸነፈው የጋናው ሀሳካስ ሌዲስ እንዲሁም በቀጠናው የማጣሪያ ውድድር የፍፃሜ ተፋላሚ የነበረው የናይጄሪያው ሪቨርስ አንግልስ በግብፁ ውድድር መሳተፋቸው ታውቋል። በ1986 የተመሰረተው ሪቨርስ አንግልስ በሀገሩ 7 የሊግ እና 8 የብሔራዊ ዋንጫ ክብሮችን ያገኘ ክለብ ሲሆን የተወዳደረበት ዞን የ2018 የሴቶች አፍሪካ ዋንጫን ያነሳ ሀገር የሚገኝበት ቀጠና በመሆኑ ዞኑ የተሰጠውን የሁለት ክለቦች የማሳተፍ ዕድል ተጠቅሞ ወደ ቻምፒየንስ ሊጉ የፍፃሜ ተፋላሚ በመሆኑ ማለፉን አረጋግጧል።

በኮሳፋ ዞን የሚገኘው እና ሦስት ጊዜ የደቡብ አፍሪካ የሴቶች ቻምፒዮንሺፕን ያሸነፈው ማሜሎዲ ሰንዳውንስ በደርባን በተደረገው ውድድር የበላይ በመሆኑ አምስተኛው አላፊ ክለብ ሆኗል። የዋናው ውድድር አስተናጋጅ ሀገር ክለብ ከሆነው እና ለ12ኛ ጊዜ የግብፅን የሴቶች የውስጥ ሊግ ውድድር ያሸነፈው ዋዲ ደግላ በቀጥታ ከዩ ኤን ኤ ኤፍ ዞን ያለፈ ሲሆን የ8 ጊዜ የሞሮኮ ሊግ አሸናፊው አስፋር ኤፍ ሲ ደግሞ የማጣሪያ ውድድሩ አሸናፊ በመሆኑ አላፊ ሆኗል። በመጨረሻወ የዩ ኤን አይ ኤፍ ኤፍ ኤ ሲ (UNIFFAC) ዞን ደግሞ የኢኳቶሪያል ጊኒ የሴቶች ሊግ የወቅቱ የዋንጫ ባለቤት እና የዞኑን የማጣሪያ ውድድር በበላይነት ያጠናቀቀው ማላቦ ኪንግ በግብፁ ፍልሚያ እንደሚኖር ተረጋግጧል።

በግብፅ አስተናጋጅነት የሚደረገው የመጀመሪያው የአህጉሩቱ ውድድር ከሦስት ወራት በኋላ ከላይ በተጠቀሱት ስምንት ክለቦች መካከል የሚደረግ ይሆናል። የውድድሩ የእጣ ማውጣት መርሐ-ግብርም ከሁለት ሳምንት በኋላ እንደሚወጣ ተመላክቷል።