አዲሱ የሀዋሳ ከተማ ዋና አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ በከተማዋ ለሚገኙ አምስት የታዳጊ ፕሮጀክቶች በርከት ያሉ የኳስ ስጦታዎችን በዛሬው ዕለት አበርክቷል፡፡
የቀድሞው የሲዳማ ቡና እና አዳማ ከተማ እንዲሁም በቅርቡ የሀዋሳ ከተማ ዋና አሰልጣኝ በመሆን በሁለት ዓመት ውል የተሾሙት አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ በሀዋሳ ከተማ በታዳጊ እግርኳስ ላይ ሲለፉ ለነበሩ አምስት ፕሮጀክቶች በርከት ያሉ ኳሶችን በስጦታ መልክ አበርክተዋል፡፡ በሀዋሳ ከተማ ሲደረግ ቆይቶ ከቀናቶች በፊት በተጠናቀቀው የሴንትራል ዋንጫ የመዝጊያ ፕሮግራም ላይ ተገኝተው የነበሩት አሰልጣኙ በታዳጊ ተጫዋቾች ላይ ሲለፉ የነበሩ ፕሮጀክቶችን ከታዘቡ በኋላ በዛሬው ዕለት በሀዋሳ ሴንትራል ሆቴል ጠርተው ከ13 ዓመት በታች ሁለት ከ15 ዓመት በታች ሁለት እና ከ17 ዓመት በታች አንድ በድምሩ ለአምስት ፕሮጀክቶች በርከት ያሉ የኳስ ስጦታዎችን አበርክተዋል፡፡
አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ለተጫዋቾቹ ካበረከቱት ስጦታ በኋላ ለሶከር ኢትዮጵያ እንደተናገሩት “ጊዜው ይህን ያስገድዳል ሁሉም ለታዳጊ ቡድኖች ትኩረት ሊሰጡ ይገባል። እኔም ይህን መነሻ በማድረግ አበርክቻለሁ። ሀዋሳ ውስጥ ያሉ ፕሮጀክቶችን ተመልክቻለሁ። በዚህም በጣም ደስተኛ ነኝ። ሁሌም ከቡድኖቹ ጎን በመቆም ታዳጊዎች እንዲፈሩ የሚቻለኝን ሁሉ ለማድረግ ተዘጋጅቻለሁ። በቀጣይም ፕሮጀክቶቹ ከበረቱ እና ከጠነከሩ የትጥቅ ድጋፍን በተጨማሪነት አደርጋለሁ።” ሲሉ የተናገሩ ሲሆን አሰልጣኙ በቀጣዮቹ ዓመታት በታዳጊ ተጫዋቾች ላይ ትኩረት ሰጥተው በክለብ ደረጃ በደንብ ለመስራት መነሳሳት እንደፈጠረላቸውም ጠቁመዋል፡፡ ስጦታ የተበረከተላቸው የፕሮጀክቶቹ አሰልጣኞችም አሰልጣኙ ላደረጉላቸው መልካም ተግባር ምስጋና አቅርበው ሌሎች የሀገሪቱ አሰልጣኞች ተመሳሳይ ድጋፍን እና ሙያዊ እገዛለን በያሉበት ሆነው ቢያደርጉ የሀገራችንን እግር ኳስ ከፍ ማድረግ ይቻላል ሲሉ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡