በኢትዮጵያ ምድብ የምትገኘው ዚምባቡዌ ጊዜያዊ አሠልጣኝ ሾማለች

ከቀናት በፊት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የተሸነፉትን አሠልጣኝ ዝድራቭኮ ሎጋሩሲች ያሰናበተው የዚምባቡዌ ብሔራዊ ቡድን ጊዜያዊ አሠልጣኝ አግኝቷል።

በ2022 የዓለም ዋንጫ ለማለፍ በምድብ ሰባት ከኢትዮጵያ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ጋና ጋር የተደለደለው የዚምባቡዌ ብሔራዊ ቡድን ሁለት የምድብ ጨዋታዎችን አድርጎ አንድ ነጥብ ብቻ ማስመዝገቡ ይታወቃል። እነዚህ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ፍልሚያዎች ጨምሮ ካለፉት 14 ጨዋታዎች አንዱን ብቻ ያሸነፉት የ55 ዓመቱን ክሮዋት አሠልጣኝ ዝድራቭኮ ሎጋሩሲችም በመጥፎ ውጤታቸው በእግርኳስ ፌዴሬሽኑ ከሁለት ቀናት በፊት ተሰናብተዋል።

በመንበሩ አሠልጣኝ ለመተካት ያልቦዘነው የዚምባቡዌ እግርኳስ ፌዴሬሽንም ኖርማን ማፔዛን በጊዜያዊነት መቅጠሩ ታውቋል። ከዚህ ቀደም ብሔራዊ ቡድኑን በጊዜያዊ እና በሙሉ ጊዜ አሠልጣኝነት ያገለገለው የ49 ዓመቱ ማፔዛ የኤፍ ሲ ፕላቲኒየም አሠልጣኝ በመሆን እያገለገለ እንደሚገኝ ይታወቃል። አሁን ግን ዳግም ሀገሩን በአሠልጣኝነት የሚያገለግልበትን ዕድል በማግኘት በቀሪዎቹ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ቡድኑን እንደሚመራ ታውቋል።