የጌታነህ ከበደ ዝውውር ጉዳይ ወቅታዊ መረጃ ?

ከፈረሰኞቹ ጋር የመለያየቱ ነገር እርግጥ የሆነው የዋልያዎቹ አንበል ጌታነህ ከበደ ቀጣይ ማረፊያው የት ይሆናል?

በሚሌንየሙ መጀመርያ በደቡብ ፖሊስ ከእግርኳስ ቤተሰብ ጋር የተዋወቀው ጌታነህ ከደደቢት ጋር የሊጉን ዋንጫ በማንሳት ለአምስት ዓመታት ተጫውቶ አሳልፏል። በማስከተል ወደ ቢድቬትስ ዊትስ አምርቶ ለሦስት ዓመታት በደቡብ አፍሪካ ቆይታ ካደረገ በኋላ ወደ ደደቢት በመመለስ ለሁለት ዓመት ቆይታ ማድረጉ ይታወሳል። በ2011 ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ  በማምራት ለቡድኑ ግልጋሎት የሰጠው ጌታነህ ቀሪ የአንድ ዓመት ኮንትራት ቢኖረውም በዲሲፒሊን ጥሰት ክለቡ ለማቆየት እንደማይፈልግ ከተገለፀ ሰነባብቷል።

ይህን ተከትሎም ጌታነህ ከበደ ቀጣይ ማረፊያው የት ይሆናል? የሚለው ጉዳይ ትልቅ ርዕስ ሆኖ ሰንብቷል። በሀገራዊ ግዳጅ ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር የቆየው ጌታነህ አሁን ምንም አይነት የብሔራዊ ቡድን ጨዋታ የሌለ በመሆኑን በእርሱ የዝውውር ጉዳይ የተለያዮ መረጃዎች እየወጡ ይገኛሉ።

ሶከር ኢትዮጵያ ዛሬ ባገኘችው መረጃ በአሁን ሰዓት ጌታነህ ከአዲስ አበባ ኤርፖርት በመነሳት ሀዋሳ ከተማ የገባ ሲሆን ከሲዳማ ቡና የክለብ አመራሮች ጋር ንግግር እያደረገ መሆኑን አረጋግጠናል። በመጀመርያ ምዕራፍ ድርድራቸው ከስምምነት እንዳልደረሱ ሲሰማ በይደር ለመነጋገር ቀጠሮ መያዛቸውንም ለማወቅ ችለናል። የድርድሩ መጨረሻ ምን እንደሚሆን የሚጠበቅ ሲሆን በዚህ ሂደት የሚኖረውን አዳዲስ ነገርሮችን እየተከታተልን የምናቀርብ መሆኑን ከወዲሁ እንገልፃለን።

ጌታነህ በ2001 በፕሪምየር ሊጉ ኮከብ ተጫዋች ሲባል ለ3 ጊዜያት ያህልም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ በመሆን ማጠናቀቁ ይታወቃል።