ከትናንት በስቲያ አስራ አንድ አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ የቀላቀለው አዲስ አበባ ከተማ አሁን ደግሞ የሰባት ነባር ተጫዋቾችን ውል ሲያራዝም ሦስት ታዳጊዎችን ከ20 ዓመት ቡድኑ አሳድጓል፡፡
ሮቤል ግርማ ውሉን አራዝሟል፡፡ ይህ የቀድሞው የኢትዮጵያ ቡና ፣ ሲዳማ ቡና እና ጅማ አባቡና የመሀል እና የግራ መስመር ተከላካይ የተጠናቀቀውን የውድድር ዘመን አዲስ አበባ ከተማን ከተቀላቀለ በኋላ ክለቡ ወደ ፕሪምየር ሊጉ እንዲመለስ በበርካታ ጨዋታዎች ላይ በመሰለፍ ጥሩ ግልጋሎት ሲሰጥ የነበረ ሲሆን በቀጣዩ ዓመትም ከክለቡ ጋር ለመቀጠል ውሉን አድሷል፡፡
ሌላኛው ተከላካይ ዘሪሁን አንሼቦም ከክለቡ ጋር መቀጠሉ እውን ሆኗል፡፡ ከዚህ ቀደም በድሬዳዋ ከተማ እና ደቡብ ፖሊስ በፕሪምየር ሊጉ ሲጫወት የምናውቀው ሲሆን የ2013 የውድድር ዘመንን ደግሞ ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር በከፍተኛ ሊጉ በመጫወት ያሳለፈ ሲሆን የመሀል ተከላካዩ በፕሪምየር ሊጉም ከክለቡ ጋር ለመቆየት ውሉን አድሷል፡፡
አሰጋኸኝ ጴጥሮስ ሌላኛው ውሉን ለተጨማሪ ዓመት ያራዘመ ተጫዋች ነው፡፡ የቀድሞው የጋሞ ጨንቻ እና ወሎ ኮምቦልቻ ተጫዋች በቀኝ መስመር ተከላካይ የተጠናቀቀውን ዓመት ለአዲስ አበባ ከተማ ጥሩ ግልጋሎት ሲሰጥ የተመለከትነው ሲሆን ያሳየውን አስደናቂ እንቅስቃሴ በፕሪምየር ሊጉ ለማሳየት ውሉን ለአንድ ዓመት በክለቡ አድሷል፡፡
አራተኛው ውሉ የታደሰለት ሳሙኤል አስፈሪ ነው፡፡ በክልል ክለቦች ሻምፒዮና ውድድር ከዚህ ቀደም ለአረካ ከተማ እና ዱራሜ ከተማ የተጫወተው ይህ የመሀል ተከላካይ በከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ በአዲስ አበባ ከተማ ጥሩ ጊዜን ያሳለፈ ሲሆን በቀጣዩ የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግም ከክለቡ ጋር ለመቀጠል ውሉ ተራዝሞለታል፡፡
በክለቡ ረዘም ያለ ቆይታ የነበረው ግብ ጠባቂው ዋኬኒ አዱኛ ፣ ተስፈኛው የመስመር አጥቂ የሺዋስ በለው እና የመሀል ተከላካዩ ነብዩ ዱላ ውላቸው የታደሱ ሌሎች ተጫዋቾች ናቸው፡፡
ክለቡ ከዚህ ባለፈ ሦስት ተስፈኛ ወጣት ተጫዋቾችን ከ20 አመት በታች ቡድኑ አሳድጓል፡፡ ኮክ ኩዌት (ግብ ጠባቂ)፣ ቧይ ጆን (የመሐል ተከላካይ) እና ምንተስኖት ዘካሪያስ (የመስመር አጥቂ) ወደ ዋናው ቡድን አድገዋል፡፡