የዓለም እግር ኳስ የበላይ የሆነው ፊፋ ወርሐዊ የሀገራት ደረጃ ከደቂቃዎች በፊት ሲያወጣ ኢትዮጵያ የደረጃ መሻሻሎችን አስመዝግባለች።
የሀገራትን የእግር ኳስ ደረጃ በየወሩ የሚያወጣው ፊፋ ከደቂቃዎች በፊት ወቅታዊውን የሀገራት ደረጃ በድረ-ገፁ ይፋ አድርጓል። ባሳለፍነው ወር በርካታ ጨዋታዎችን (የነጥብ እና የአቋም መፈተሻ) ያደረገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም በሀምሌ ወር በወጣው ደረጃ ከነበረበት 137ኛ ደረጃ ወደ 134ኛ ከፍ ማለቱ ተመላክቷል። ብሔራዊ ቡድኑ ባሳለፍነው ወር ከተሰጠው 1079.41 ነጥቦች 13.33 ነጥቦችን በመጨመር በአጠቃላይ በ1092.74 ነጥቦች በማግኘት ከዓለም 134ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ባሳለፍነው ወር 54 ሀገራት በሚገኙበት አህጉር 40ኛ ደረጃ ላይ የነበረው ብሔራዊ ቡድኑም የቶጎ አቻውን በልጦ በአህጉሩ አንድ ደረጃን በማሻሻል 39ኛ ደረጃን መያዙ ታውቋል።
ለበርካታ ወራት የዓለም እግር ኳስ ቁንጮ ሆና የዘለቀችው ቤልጂየም አሁንም በ1832.33 ነጥቦች አንደኛ ደረጃ ላይ ስትቀመጥ ብራዚል ደግሞ 1811.73 ነጥቦች በመያዝ በሁለተኝነት ዘልቃለች። ባሳለፍነው ወር አራተኛ ደረጃ ላይ የነበረችው እንግሊዝ በበኩሏ የወቅቱን የዓለም ዋንጫ አሸናፊ ፈረንሳይን በመብለጥ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
በአህጉራችን አፍሪካ ደግሞ ከዓለም 20ኛ የሆነው የሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን ቱኒዚያ እና አልጄሪያ በማስከተል የአፍሪካ ቁንጮ መሆኑን ቀጥሏል።